የማር ምርት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈረመ

189
ሰኔ13/2011 የአገሪቷን የማር ምርት ጥራቱ ተጠብቆ በአለም ገበያ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ። ማርን እንደ ቡና በጣዕማቸው የሲዳማ ማር፣ የጎጃም ማር እና የትግራይ ማር የሚልና የራሱ መለያዎችን በመስጠት በአለም ገበያ ማስተዋወቅ ከስምምነቱ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው። ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ የምርቱን ጥራት ማሻሻል፣ የወጪ ንግዱን ማበረታታትና የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት አላማ ያደረገ ነው። ለስኬቱም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  ጋር በትብብር ለመስራት ዛሬ ተፈራርመዋል። ምርቱ ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡትን 9 መመዘኛዎች ማሟላቱን  ለማረጋገጥም የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት እና ብሌስ የምግብ ላቦራቶሪ አገልግሎት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላቦራቶሪዎች ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሊድ ቦምባ “ምርቱ ወደ ውጭ ከተላከ በኋላ እንዳይመለስ ላቦራቶሪዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ የጥራት መስፈርቶች በመታገዝ  ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ ብቻ ወደ ውጭ ይላካል” ነው ያሉት። አያይዘውም ላቦራቶሪዎቹ የተመረጡት በአለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ፣ ከኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽህፈት ቤት ባገኙት መረጃ እና በአለም ደረጃ በተሰጣቸው ሰርተፊኬት እንደሆነም ገልጸዋል። አገሪቷ በማር ምርቷ በአለም ዘጠነኛ በአፍሪካ አንደኛ መሆኗን ተከትሎ ስምምነቱ የማር ምርት ጥራቱን እንዲጠብቅ  ለማስቻል ላብራቶሪዎችን በገንዘብና በአቅም ግንባታ መደገፍ የሚያስችል ነውም ተብሏል። ለአምራቾች ደግሞ ከአመራረት ጀምሮ እስከ መጨረሻ ባሉ ሂደቶች በጥራት ማምረት እንዲችሉ ትምህርትና ድጋፍ ከመስጠት አንስቶ የገበያ ትስስር እንደሚመቻችላቸውም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል። ለዘርፉ ማደግም 7 ሺ አርሶ አደሮችን ያቀፈ ፕሮጀከት መዘርጋቱ በዚሁ ወቅት ተገልጿል። በማር ማነብ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የማምረት አቅማቸውን ለመጨመርም ሰባት የዘርፉ ኢንተርፕራይዞችን በመለየት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቢዝነስና የማኔጅመንት ስልጠና ለመስጠት መሆኑም ተገልጿል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው አገሪቷን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ የዘርፉን ኢንተርፕራይዞች የማሳደግና አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በዓመት 500 ሺ ቶን የማር ምርት እንደሚመረት የተገኘው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም