የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ለዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጠቃሚ ግብአቶች ተሰብስቦበታል

71
ሰኔ 13/2011 የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምትከተላቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጠቃሚ ግብአቶች የተሰበሰበበት እንደሆነ ተገለጸ። ከሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደው የመጀመሪያው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዛሬ ተጠናቋል። "የውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለአዲሲቷ የተስፋ አድማስ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በአጠቃላይ 1 ሺህ 300 ገደማ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የውሃና ኢነርጂ ሳምንትን መጠናቀቅ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሳምንቱን ማካሄድ ያስፈለገበት አላማ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብቶች ወደ ተለያዩ ልማቶች በመቀየር ተጠቃሚ በምትሆንበት ሁኔታ ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት ማድረግና ሀሳቦችን ለመለዋወጥ ነው። በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ በተካሄዱ የውይይት መድረኮች እና የጎንዮሽ ውይይቶች 74 የሚሆኑ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው አመልክተዋል። ከዚህም አኳያ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በተደረጉ ምክክሮች ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምትከተላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ግብአቶች መሰብሰባቸውን ተናግረዋል። በተደረጉት ውይይቶች የልማት አጋሮች በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የሚሰሩትን ስራዎች ያቀረቡበት እና የሚሰሩ ስራዎች በቀጣይ ይበልጥ በቅንጅትና በቁርኝት መስራት እንደሚገባ የፋይናንስ ተደራሽነቱን ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ እንደተቀመጠም ጠቅሰዋል። ሳምንቱ የውሃና ኢነርጂ ዘርፉ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚያ ሽግግር ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት የተሰጠበት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ለመሳካት የውሃና ኢነርጂ አቅርቦትን መሳፍ በጣም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተሰምሮ ያለፈበት ነው ብለዋል። በውሃ መስኖና ኢነርጂ ዘርፎች ውስጥ በሚገኙ ባለድርሻ አካላት ውስጥ በተበጣጠሰ መልኩ የሚሰሩ ስራዎችን በተደራጀ መልኩ መስራት እንደሚገባም በውይይቶቹ ላይ መገለጹን ተናግረዋል። በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ማስተዳደርና ተጠያቂነት ላይም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ከተሳታፊዎች የተነሳ ሀሳብ እንደሆነም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት። እ.አ.አ በ2024 በኢትዮጵያ አሁን ያለውን በየቦታውና በየመንገዱ ያለውን መጸዳዳት በማስቀረት የንጽህና አጠባበቅን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክከር ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል። በሁለተኛው የ'ዋን ወሽ' መርሃ ግብር፣የወጣቶች መስኖ ልማት መርሃ ግብር፣ ብርሃን ለሁሉ ሁለተኛው የኤሌትሪፊኬሽን መርሃ ግብር፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይም ውይይቶች ተካሄደዋል ብለዋል። ኮይሻና ሌሎች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደረጉባቸው ስላሉ የታዳሽ ሃይል ልማት ፕሮጀክቶች፣ የ4 ቢሊዮን የዛፍ ቸግኞችን በመትከል ከተሞችንና ገጠር አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴ የማሸጋገር እቅድና ሌሎች መርሃ ግብሮች ላይ ምክክር መደረጉን አመልክተዋል። በውሃ መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም በአውደ ርዕይ መልክ መቅረባቸውን አመልክተው በአጠቃላይ የውሃና የኢነርጂ ሳምንቱ ውጤታማ ነበር ማለት እንደሚቻል ጠቅሰዋል። ዛሬ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንቱ ማጠቃለያ ቀን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት እና የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ተሳታፊዎች በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን አዲስ አበባ ዙሪያ ሱልልታ ወረ ሊሎ ጨበቃ እና ቆሬ ሮባ ቀበሌ ገበሬ ማህበሮች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል። በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የቀበሌ ገበሬ ማህበሮቹ ነዋሪዎች እና የሰላሌ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተሳትፈዋል። በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ በተካሄዱት የውይይት መድረኮች የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት፣ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት፣ ከዩኒቨርስቲዎችና ከምርምር ማዕከላት የተወጣጡ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍ፣ አጋር ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና ሌሎች ተቋማት ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም