በአዲስ አበባ የንግድ አሰራሩን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተነገረ

50
አዲስ አበባ ሰኔ13/2011 በከተማ አስተዳደሩ የንግድ ስርዓቱን አሰራር ለማሻሻልና ለማዘመን እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከንግድ ጋር ተያይዞ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችሉ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጸ። ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ውድድርና የግብር አከፋፈል እንዲኖር በማድረግ ነጋዴው በፍቃደኝነት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ያስችላል ብለዋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ይህን ያሉት ዛሬ ከከተማዋ የንግዱ ማህበሰረብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ተሳታፊ ነጋዴዎቹም ከንግዱ ጋር ተያይዞ አሉ ያሉትን ችግሮች አንስተዋል። መንግስት በንግድ ላይ ያለውን የአሰራር ስርዓት ማበጀት እንዳለበትና የራሱን ሰራተኞች በአግባቡ መቆጣጠር እንደሚገባውም አውስተዋል። ነጋዴዎቹ በከተማዋ ከግብር ስወራ፣ ከኮንትሮባንድ ችግርና የኦዲት ስራ በትክክል አለመከናወን ጋር ችግሮች መኖራቸውን አውስተው፤ አስመጪዎችና ላኪዎች በህገወጥ ንግድ መሳተፋቸውና ግብር በአግባቡ አለመክፈላቸውንም አንስተዋል። መንግስት በትንንሽ ነጋዴዎች ላይ ብቻ በማተኮር ትልልቆቹን ችላ በማለቱ ትላልቆቹ ነጋዴዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ እየከፈሉ አይደለም የሚሉ ጥያቄዎቸንም ሰንዝረዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንግስት ነጋዴውን ወደ መቅጣት ከመግባቱ በፊት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በተለያየ ዘዴዎች መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል። አዳዲስ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች ለነጋዴው ከመቅረቡ በፊት የግንዛቤ ስራ መስራት ያስፈልጋል፤ ይህ ሲሆን ነጋዴው በተገቢው መንገድ ግዴታውን ይወጣልም ብለዋል። ምክትል ከንቲባው ጥያቄውን ተከትሎ በሰጡት ምላሽ "ከተማ አስተዳደሩ የንግድ ስርዓቱን በማዘመን ላይ እንደሚገኝና ይህም ከንግድ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል። የንግዱ ማህበረሰብም የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል አገራዊ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል። በህገ ወጥ ንግድ፣ በኮንትሮባንድ እና በሌሎች ህገወጥ ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ነጋዴዎችን ህብረተሰቡ የማጋለጥ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል። በመዲናዋ ህጋዊ ነጋዴዎችን ለማበረታታትና ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባልም ከፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጋር በመስራት ከ3 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲነሳላቸው መደረጉን እንደ አብነት አንስተዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ቁጥጥር ኃላፊ ሀሰን ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፖሊስም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ህገወጥ ነጋዴዎችን የመከላከል ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ፖሊስ የሚመጡትን ጥቆማዎች መሰረት አድርጎ እርምጃ ይወስዳል ያሉት ኃላፊው ፍትሃዊ የሆነ አሰራር በመከተል እንደሚሰሩም አክለዋል። ህጋዊ ነጋዴዎችም በህገወጥ መንገድ የሚሰሩትን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡ የሚሰራውን ስራ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም