ቄሮዎች አገሪቷ በተያያዘችው ሁሉን አቀፍ የለውጥ እንቀስቃሴ ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

98
አዳማ ሰኔ 13/ 2011የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) አገሪቷ የተያያዘችውን ሁሉን አቀፍ የለውጥ እንቀስቃሴ በውል ተገንዝበው ድርሻቸውን እንዲወጡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አስገነዘቡ። 12ኛው የኦሮሞ ወጣቶች ኮንፈረንስ በፖለቲካ  የተገኘው ድል በኢኮኖሚ ሪፎርም መደገፍ አለብን በሚል መሪ ቃል ዛሬ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት ወጣቶች ለለውጡ ቀጣይነት ያላቸው የማይተካ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል። በፖለቲካ የተገኘው ድል በኢኮኖሚ ሪፎርም በፍትህና ዴሞክራሲ እንዲደገፍ ድርሻቸውን እንዲወጡም  ጠይቀዋል። አገሪቱ የጀመረችውን ሁሉ አቀፍ ለውጥ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ  እንዲያሸጋግሩ ያሳሰቡት ኃላፊው፣በተለይም እየሰፋ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ለፍትህ፣ ለዴሞክራዊና እኩልነት በር የከፈተ በመሆኑ ድሉ ጠብቀን ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ አመልክተዋል። ''ማንኛውም አካል በፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን በሕዝብ የመጣውን ለውጥ ማጣጣልና መቀልበስ እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባል ያሉት አቶ አዲሱ፣ ሕዝቡና ወጣቶች ለውጡን በጸኑ መሠረት ላይ ለማቆም መረባረብ ይጠበቅበናል'' ብለዋል። የሕዝቦችን አንድነት በመጠበቅ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲተገበር ወጣቱ ዘላቂ ሰላምን በመጠበቅና በልማት ተሳትፎውን እንዲያጠናከር ያስገነዘቡት ኃላፊው፣ከፖለቲካው ባሻገር የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያሻ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል ሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙና አህመድ በኢኮኖሚ ያልተደገፈ ፖለቲካ ብቻውን የትም ስለማይደርስ የክልሉ ወጣቶች በአገራዊ ለውጥ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በትምህርት ፣በሥራ ፈጠራና በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ረገድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም፤ ትኩረት ተሰጥቶ  የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኦዴግ)ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው ወጣቱ አገሪቷ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገርና ሁሉም ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲተገበር ሚናውን እንዲጫወት አሳስበዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም