ከአዲሱ መሪ ፕላን ጋር የሚቃረኑ ልማቶች በጥናት መልስ ያገኛሉ

132
ሰኔ 13/2011 በዘጠነኛው የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ላይ ህጋዊ የሆኑና ከአዲሱ መሪ ፕላን ጋር የሚቃረኑ ልማቶች በጥናት መልስ እንደሚያገኙ የከተማዋ ፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ። በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ የተደረገው ማስተር ፕላን እያደገ የሚሄደውን የከተማዋን ህዝብ ፍላጎት መመለስ አለመቻሉን ምሁራን ይናገራሉ። የከተማ አስተዳደሩ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ደረጄ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማዋ የነዋሪዎቿን  የእድገት ደረጃ በሚመጥን መልኩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ 10ኛው የተቀናጀ መሪ ቅድ መተግበር ከጀመረ ሶስት ዓመት ሆኖታል። “አሁን እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች አዲሱን መሪ ፕላን መሰረት ያደረጉ ናቸው” ያሉት ኮሚሽነሩ በዘጠነኛው መሪ ፕላን ህጋዊ ሆነው ከአዲሱ ጋር የሚቃረኑ ልማቶችም በጥናት መልስ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። “ፕላኑ በልማት ምክንያት ነዋሪዎችን ከቦታቸው በማፈናቀል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚዳርግ  አይደለም” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የአዲስ አበባ ታሪካዊ መገለጫዎችም ለከተማዋ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ታሳቢ ማድረጉን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተሾም በበኩላቸው “ለከተማዋ በተለያየ ጊዜ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ቢደረግም እያደገ የሚሄደውን የህዝብ ፍላጎት  እየመለሰ አልነበረም” ይላሉ። ከተማዋ ከመቶ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት ስትቆረቆር የተፈጥሮ ሚዛኑ የተጠበቀ ቢሆንም፤ በህዝብ ቁጥር መጨመርና በሌሎች ምክንያቶች ይዘቱ ተጠብቆ ባለመቀጠሉ ይሄንን አጣጥሞ መምራት የሚያስችል የተቀናጀ ፕላን መጠቀም አስገዳጅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “ከተሜነት የእድገት ምልክት በመሆኑ ተፈጥሮን እየገደልን ሳይሆን አጣጥመን መምራት ያስፈልጋል ” በማለትም ይገልጻሉ። ፕላን የሚዘጋጀው ዘመናዊ የከተማ ግንባታን ከተፈጥሮአዊ ይዘት ጋር ለማስማማት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ  የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህርና አርኪቴክት ሙሉጌታ በቀለ ናቸው። በዚህ መነሻ “አዲስ አበባ ከምስረታዋ ዘመናዊ ፕላንን ተከትላለች ባይባልም በየጊዜው የሚቀየሱት ፕላኖች በተገቢው ላለመተግበራቸው የኢኮኖሚና የተቋማት የማስፈጸም አቅም ማነስ ምክንያት ናቸው” ይላሉ፡፡ “ፕላን ሲሰራ መሰረተ ልማትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በጥናት በመለየት የአካባቢ ጥበቃን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታን ታሳቢ ማድረግ ይገባል” ሲሉም መክረዋል፡፡ “በከተማዋ አሁን ያለው መሰረተ ልማትና የመዝኛና ስፍራ የህዝቡን ቁጥር አይመጥንም” ያሉት መምህር ሙሉጌታ፤ መንገዶች ለአካል ጉዳተኞችም ሆነ ለእግረኞች ምቹ እንዳልሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ “በከተማዋ ፕላንን በአግባቡ መተግበር አለመቻል የሀብት ብክነትና የማህበራዊ ችግርን አስከትሏል” ብለዋል። “የተቀናጀ የከተማ ፕላን ስለ ነገ አሻግሮ የሚያይና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ሊሆን ይገባል”  ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፤ “የከተማችንን እድገት ፕላን ጠብቀን መምራት ከቻልን ለዜጎች ምቹና ህገወጥ አሰራርን መከላከልም ያስችላል” ብለዋል፡፡ አዲሱ ማስተር ፕላን በቀደመው ላይ የታዩ ጉድለቶችን በመለየትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ በቅይጥ የሚሰሩ  አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከመኖሪያ ቤት መለየቱን በኮሚሽኑ የፕላን አፈጻጸም ክትትልና ግምገማ ባለሙያ ደራርቱ ደንደና ተናግረዋል። በተጨማሪም የትራንስፖርት አቅርቦትን ከአሽከርካሪ ተኮር ወደ እግረኛ ከማድረግ ባለፈ የህንጻ ከፍታ  መጨመርና አረንጓዴ ስፍራዎች በአዲሱ ፕላን መካተታቸውንም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በ1886 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ ከተዘጋጀው የአሰፋፈር እቅድ አንስቶ የአሁኑ ለአስረኛ ጊዜ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ ነው። አስረኛው የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ መሪ ፕላን ጸድቆ ተግባር ላይ መዋል ከጀመረም ሶስት ዓመታትን  አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም