የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት "ኅብረተሰቡ የፓልም ዘይትን እንዳይጠቀም" አላልኩም አለ

170
ሰኔ 13/2011 የፓልም ዘይትን አስመልክቶ በአንዳንድ ሚዲያዎች የተላለፈው ዘገባ ኢንስቲትዩቱ ከገለጸው ውጪ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሰጠው መግለጫ እንዳለው፤ ፓልም ኦይል እየተባለ የሚጠራውን ዘይት በየቀኑ መጠቀም ዘይቱ በውስጡ ካለው ሳቹሬቲድ ፋቲ አሲድ አንፃር በረዥም ጊዜ መጠቀም የኮልስትሮል መጠንን ከፍ ያደርጋል ተባለ እንጂ ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም አላልከኵም ብሏል። በአንዳንድ ሚዲያዎች "ኢንስቲትዩቱ  የሚረጋውን ዘይት ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም አስጠነቀቀ" ተብሎ የተላለፈው ዘገባ "ከእውነታው የራቀ" መሆኑን የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛህኝ ተስፋዬ አስረድተዋል። ኢኒስቲትዩቱ የሚረጋውን የፓልም ዘይት ጨምሮ በ16 የፈሳሽ ዘይቶች ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥናት ማድረጉን የተናገሩት በጥናቱ ላይ የተሳተፉት የምግብ ሳይንስና የሥነ ምግብ ምክትል ዳሬክተር ዶ/ር አረጋሽ ሳሙኤል፤ የሚረጋውን ዘይት ሁልጊዜ መጠቀም በጊዜ ሂደት ልክ ጮማና ቅቤ የኮልስትሮል መጠን እንደሚጨምሩት የረጋ ዘይቱም የኮልስትሮል መጠንን ይጨምራል ብለዋል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ የረጋ ዘይት አጠቃቀሙን ሊያስተካክል ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል። የረጋ ዘይት አጠቃቀሙን ያስተካክል ሲባል እንዴት ነው ተብለው የተጠየቁ ዶ/ር አረጋሽ፤ አንድ ሰው የረጋውን ፓልም ዘይት በቀን ቢበዛ ሦስት የሾርባ ማንኪያ ብቻ መጠቀም ይገባዋል ብለዋል። ይህም የዓልም የጤና ድርጅት መስፈርት መሆኑን አብራርተዋል። ጥናቱ ለጤና ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ተልኮ መንግሥት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራው ግብረ ሃይል አቋቁሞ የሚረጋው ዘይት በሌላ እንዲተካ እያስጠና መሆኑንም በመግለጫው ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ከውጪ በሚገባው ፓልም ዘይትን በየጊዜው ሂደት የኮልስትሮል መጠንን እንደሚጨምር በጥናት ማረጋገጡን መግለጹ ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም