ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሻለ የአሰራር ስረ ዓት እየተከተለ ነው ተባለ

44
አዲስ አበባ ሰኔ13/2019የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በተሻለ አሰራር ለደንበኞች  ተገቢውን  አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት ለተሻለ ውጤት መስራት እንዳለበት ምክር ቤቱ አሳስቧል። በምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኮፖሬሽኑ መደበኛ የመሰክ ምልከታ አድርጓል። የቋሚ ኮሚቴው የቡድን መሪ አቶ መልካሙ ሶሬ እንደገለጹት ኮፖሬሽኑ እያደረገ ያለው የስራ እንቅስቃሴ ጥሩ ጅምሮች አሉት። በተለይም ሰራተኛው ለቤቶቹ ያለው የኔነት ስሜት፣ የመልካም አስተዳዳር ችግር ለይቶ ለመፍታት የሚያደርገው ሥራ፣ ቤቶቹን በመኖሪያና በንግድ ቤት ለይቶ መረጃዎችን በዲጂታል ማደራጀት መጀመሩ ከመልካም ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ውል ያላደሱ ሰዎች ውል እንዲያድሱ፣ የአመራሩና የሰራተኞው ግንኙነት ጥሩ መሆኑ፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ውል ሲያድሱ የሚያደርገው ልዩ ትኩረት፣ ቅሬታ አቅራቢዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላው ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል። ይሁንነና የተገልጋይ እርካታን የሚጨምሩ የጥገና ሥራዎችን፣ የቤት አሰጣጥና ቤቱ የተሰጣቸው ሰዎች በአገልግሎቱ እንዲረኩ የሚያደርግ ስራ ላይ በትኩረት መስራት ይገባዋል ተብሏል። የህግ ክፍል አቅም ማጎልበት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራን ማሳደግ፣ ተቋሙ ሳያውቅ ቤቶች እንዳይፈርሱ፣ ጥገና ሳያልቅ ቁልፍ ያለመስጠት፣ ቤት የሚለቁ ሰዎች ቤቶቹን ሳይበላሹ እንዲያስረክቡና የጥገና ባለሙያዎችን ሟሟላት የቀጣይ ትኩረቱ ሊሆን ይገባል ተበሏል። በኮፖሬሽኑ የቅርንጫፍ 4 ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አፀዱ ረጋሳ በበኩላቸው ተቋሙ የጥገና ስራ የሚያስፈልጋቸውን፣የመልካም አስተዳዳር ችግር ያለባቸውን፣ወል ማስፈረም፣ የጥገና ፍቃድና የደንበኛ አገልግሎትን ለይቶ እየሰራ ይገኛል። በመሆኑም የቤቶች መረጃ ዲጂታል እንዲሆን፣ የቤት ውሎች በኮምፒውተር የታገዘ የማድረግ፣ ቅሬታ ያለባቸው ደንበኞች ችግር የመፍታት ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘንድሮ ዓመት ከህግ አግባብ ውጪ የተያዙ 50 ቤቶችን ለማስመለስ አቅዶ 54 ያስመለሰ ሲሆን ውል መፈራረም የሚገባቸው ከ1 ሺህ 471 የንግድ ቤቶች ውስጥ ደግሞ 34 ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ ውል መፈረም ችለዋል ብለዋል። ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በስሩ 3 ሺህ 821 ቤቶችን የሚያስተዳዳር ሲሆን 2 ሺህ 350ዎቹ የመኖሪያ ሲሆኑ 1 ሺህ 471 ደግሞ የንግድ ቤቶች መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም