ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት ዕለት በናይሮቢ ይከበራል

209

ሰኔ 12 / 2011ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት እና የኢትዮጵያ ኤምባሲው መሰረት የተጣለበት 55ኛ ዓመት በናይሮቢ ይከበራል።

ዕለቱ በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ሰኔ 19 እና 20 ቀን 2011 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ኤምባሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያና ኬንያ የተወጣጡ ባለሃብቶች የሚሳተፉበት የቢዝነስ ፎረም ዕለቱን በማስመልከት የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያ ምርቶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ለእይታ እንደሚቀርቡና ከባለሃብቶች ጋር ትስስር እንደሚፈጠር መግለጫው አመልክቷል።

በፎረሙ ላይ 500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበትም ተመልክቷል።

በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲና በኤምባሲው የፎቶና የስዕል ኤግዚቢሽን የሚቀርብ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባህል፣ ሃብት እና እሴት ለኬንያውያን የሚተዋወቅበት ዕድል እንደሚፈጥር ይገመታል።

በተጨማሪም በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ፣ የኢኮኖሚያዊ ግንኙነትና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም የፓናል ውይይት ይካሄዳል።

ከናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች የሚሳተፉበት በኢትዮጵያና ኬንያ ግኑኝነት፣ በላሙ ፕሮጀክት ፋይዳና ሂደት እንዲሁም በኢትዮጵያ የንግድ ኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚያተኩሩ አምስት የጥናት ወረቀቶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም እና የናይሮቢ ዩንቨርሲቲ በመወከል ዶክተር ጆይ ኪሩ ኦሪንዲ የዩንቨርሲቲው የህዝብ ግኑኝነት ጉዳይ ዳይሬክተር ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ውይይት የህዝብ ለህዝብ ትውውቅ እንዲጠናከር በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።

አምባሳደር መለስ የኬንያ ባንኮችና ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ባሳየችው አዲስ ለውጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

የናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ጆን ኦሪንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀ የጠበቀና የማይዋዥቅ የመንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ግንኙነቱን ለማሳደግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተቋማት ጋር ተባብረው መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡት የጥናት ወረቀቶች የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያለፈበትን ሂደት፣ ተስፋና ዕድሎችን ያሳያሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ኬንያውያን ስለ ኢትዮጵያውያና ህዝቦቿ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዕድል እንደሚፈጥር ኤምባሲው አስታውቋል።

በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ በኩል ተከታታይ የጋራ መድረኮችን ለማዘጋጀት እንዳሰቡ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከ55 ዓመት በፊት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና የቀድሞ የኬንያ መሪ ጆሞ ኬንያታ አማካኝነት የኤምባሲዋን መሠረት የጣለችው ሰኔ ወር 1956 ዓ.ም ነበር።