ለሃጂ ጉዞ ባለፉት 10 ቀናት ብቻ 12 ሺህ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በባንክ ገቢ አድርገዋል

153

ሰኔ 12/2011 ለሃጂ ጉዞ ባለፉት 10 ቀናት ብቻ 12 ሺህ ሰዎች ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

በምክር ቤቱ የስራ አመራር ቦርድ የሃጂና ኡምራ አገር ውስጥ አስተባባሪ ሸህ አንዋር ሙስጠፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በተሰጠው ኮታ መሰረት እስካሁን በቂ የሰው ሃይል ገንዘቡን በባንክ  ገቢ አድርጓል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ለሃጂ ጉዞ በሚል ህዝበ ሙስሊሙ ገንዘብ ወደ ጠቅላይ ምክር ቤቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ እንዳያደርግ አሳስበዋል።

የሳኡዲ መንግስት ለኢትዮጵያውያን የሃጂ ተጓዦች የሰጠው ኮታ 8 ሺህ ብቻ መሆኑን ያስታወሱት ሸህ አንዋር ዘንድሮ 4 ሺህ ተጨማሪ ሃጃጆችን እንድፈቅድላቸው ተጠይቋል።

የሳኡዲ ሃጂ ሚኒስቴርም የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ እንደሚፈቅድ ስለታመነ በድምሩ 12ሺህ ተጓዦች ከሁለት ወር በኋላ ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

በመሆኑም ባለፉት 10 ቀናት ለሃጂ ለተፈቀደው ኮታ በቂ የሰው ሃይል በጠቅላይ ምክር ቤቱ የባንክ አካውንት ገቢ በማድረጉ ከዛሬ ጀምሮ ሌሎች ሰዎች ገቢ እንዳያደርጉ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጎን ለጎን ገንዘብ በባንክ ገቢ ያደረጉትን ሁሉ ለሃጂ ብቁ መሆናቸውን እያጣራ በመመዝገብ ላይ መሆኑም ታውቋል።

እንደ ሸህ አንዋር ገለፃ እስካሁን በተደረገው ማጣራት 5 ሺህ ተጓዦች የሃጂ ቁጥር ተሰጥቷቸው ለጉዞ ዝግጁ ሆነዋል።

በማጣራት ሂደቱ ገንዘባቸውን ገቢ ካደረጉት መካከል የሃጂ መስፈርቱን የማያሟሉ ሰዎች ከተገኙ ገንዘባቸው ተመልሶ እድሉን ሌሎች እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።

ለዚህም በሌላ ጊዜ በሚሰጥ መግለጫ የሚያሳውቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ለ1 ሺህ 440ኛው ዓመተ ሂጂራ የሃጂ ጉዞ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሳኡዲ ጉዞ የሚጀመር መሆኑ ታውቋል።