ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

101
ሰኔ 12/2011 ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ የማነ ገብረአብ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህንና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ የማነ ገብረአብን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው  አነጋግረዋል። ኃላፊዎቹ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላጅ አባት ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹበትን ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አድርሰዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ መልኩ የተጀመረውን የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውም ተገልጿል። ከምክክሩ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ተከላ አካሂደዋል። የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የገለጹት የፕሬዚዳንቱ አማካሪ የተጀመረው ግንኙነት ይበልጥ በህዝብ ለህዝብ ትስስር በሚዳብርበት ሁኔታ ላይ መምክራቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ከሁለቱ አገሮች ህዝቦች በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ትስስር አዲስ መነቃቃት ይዞ መምጣቱንም አማካሪው አብራርተዋል። ሰላምን መገንባት ጊዜ የሚጠይቅ ስራ ነው ያሉት አቶ የማነ ገብረአብ፤ በቀጣይ የሁለትዮሽ  ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ኤርትራ ዝግጁ መሆኗን አውስተዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም