የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ሊመሰርት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ሊመሰርት ነው
62
ሰኔ 12/2011 የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ይመሰረታል ተባለ። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ10 ሺህ የሚልቁ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ስልጠና ትምህርት የተከታተሉ የወጡ ባለሙያዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ከእነዚህ ባለሙያዎች በተጨማሪ በልምድ የሚሰሩና አጫጭር ስልጠና በመውሰድ በስፖርት ላይ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎችም ይገኛሉ። በዚህ የማህበሩ ምስረታ ላይ በስፖርቱ ዙሪያ የሚሰራ ማንኛውም ባለሙያ መካፈል ይችላል ተብሏል። የዚህ ጉባኤ ምስረታ አስተባባሪ አቶ ቢልልኝ መቆያ ''ዓላማው የባለሙያዎችን መብት ማስከበርና ባለሙያዎች ያላቸውን እውቅተና ግንዛቤ ለአገሪቱ ማበርከት የሚገባቸውን ያህል እንዲያበረክቱ ለማድረግ ነው'' ብለዋል። የማህበሩ መመሰረት በተበታታነ መልኩ የሚታየውን የዘርፉ ባለሙያዎችን አስተዋጽኦ በማቀናጀት በስፖርቱ ዘርፍ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል። የስፖርት ሳይንስ ማህበራት በዓለም ላይ የሚታወቅና ለማህበረሰብ ጤና በስፋት እንደሚሰሩ የሚታወቅ ነው። የአውሮፓውያን የስፖርት ሳይንስ ኮሌጅ፣ የብሪታኒያ ስፖርትና የአካል ብቃት ሳይንስ (ቤዝስ)፣ የአሜሪካ ስፖርት ህክምና ኮሌጅና የአውስትራያ አካል ብቃትና ስፖርት ሳይንስ (ኢሳ) የታወቁ የስፖርት ሳይንስ ማህበራት ናቸው።