በጋምቤላ ከ18 ሺህ በላይ ተማሪዎች የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰዱ ነው

69
ጋምቤላ ሰኔ 12 / 2011 በጋምቤላ ክልል ከ18 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት ፈተናው እየተሰጠ ያለው 11 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጨምሮ በ167 የፈተና ጣቢያዎች ነው፡፡ ከጠቅላላ ተፈታኞች መካከል አራት ሺህ የሚሆኑት ተፈናቃዮች መሆናቸውንም አስረድተዋል። ከተፈታኞቹ  6ሺህ 600 ያህሉ ሴቶች ናቸው።ከነዚህም 757 ስደተኞች ናቸው።እስከ ፊታችን ዓርብ ድረስ በዘጠኝ    ትምህርት ዓይነቶች ፈተና ይሰጣል። ፈተናው በሰላማዊና ኩረጃን ባስወገደ መልኩ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ፈተናውን ስኬተማ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ የፈተና ኮማንድ ፖስት እስከ ፈተና ጣቢያ ድረስ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም 519 የሰው ኃይል መሰማራቱን ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮ ተፈታኞች ቁጥር ከአምናው በሁለት ሺህ ብልጫ ማሳየቱን ኃላፊው አስታውቀዋል። ክልሉ ሰሞኑን  የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎችን ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም