የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ከሚጥሱ ድንጋጌዎች የፀዳ መሆኑ መረጋገጥ አለበት ተባለ

256

ሰኔ 12/2011 በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ከሚጥሱ ድንጋጌዎች የፀዳ ይሆን ዘንድ በትኩረት መታየት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።

አዲሱ አዋጅ ‘የጸረ -ሽብር አዋጁ’ በሚል በ2005 ዓም ወጥቶ ስራ ላይ የዋለውንና ዜጎችን ሰብአዊ መብት የጣሰ፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ያጠበበ ነው የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየውን ነባሩን አዋጅ የሚተካ ነው።

በጠቅላይ አቃቢ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረጽ ዳሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ለኮሚቴው አባላት በሰጡት ማብራሪያ አዋጁን ለማዘጋጀት በተደረገው ጥናት በነባሩ የጸረ-ሽብር አዋጅ 652 ክፍተት ያለባቸው በርካታ ድንጋጌዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።

በአዋጁ ዜጎች ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የወንጀል ተግባር አድርገው የሚመለከቱ አያሌ የህግ ድንጋጌዎች ያሉበት መሆኑም በጥናቱ መታየቱን አመልክተዋል።

በዚህም ግለሰቦች መብቶቻቸውን በመጠቀም በሚፈፅሙት ተግባር የሽብር ወንጀለኛ ተደርገው ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲደርስባቸው አድርጓል።

“በመሆኑም ራሱን የቻለ፣ ደረጃን የጠበቀ፣ የአለም አቀፍ ተሞክሮን ያካተተ፣ በተለያዩ የመንግስት አካላት የሚወጡ ህጎችን ታሳቢ ያደረገ የሽብር ወንጀል ማርቀቅ በማስፈለጉ ነባሩን የሚሽር አዲስ አዋጅ ተዘጋጀቷል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም “የጸረ ሽብር አዋጅ” ይሰኝ የነበረው አዋጅ አዲስ በተረቀቅው አዋጅ “የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” ወደሚል ስያሜ ተቀይሯል ሲሉም አመልክተዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግም ከቋሚ ኮሚቴዎችና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኩል ‘ተጨማሪ ማብራሪያና ማስተካከያ ያስፈልጋቸዋል’ ባሏቸው አንቀጾች፣ ድንጋጌዎችና ትርጓሜዎች ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም  የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን  ከሚጥሱ ድንጋጌዎች የፀዳ መሆኑ መረጋገጥ አለበት የሚለው ከምክር ቤቱ አባላት በስፋት የተነሳ ጉዳይ ነው።

ከዚሀም ሌላ በረቂቅ አዋጁ ‘ማደም፣ መዛት፣ መሰናዳት’ የሚሉትና ሌሎች ትርጓሜዎች አሻሚ በመሆናቸው ግልፅ ትርጉም ሊቀመጥላቸው ይገባል የሚል አስተያየት ከአባላቱ ቀርቧል።

በነባሩ የጸረሽብር አዋጅ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ግለሰብ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለቀናት ይቆይ እንደነበር በማንሳት በአዲሱ አዋጅ የሚቀርብበት ጊዜ በግልጽ እንዲቀመጥም ሀሳብ ተሰጥቷል።

የወንጀል ቅጣትን በተመለከተ ወንጀሉን የፈጸመ ሰው ከ18 እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ የሞት ቅጣትን በአማራጭነት ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ የሚለው ሌላው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ነው።

በነዚህና ሌሎች በረቂቅ አዋጁ የተቀመጡ አንቀጾችና ትርጓሜዎች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ወስደው በማሻያው እንዲያዩ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አሳስበዋል።

የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በረቂቅ በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ ቃላት አዋጁ ተግባራዊ ሲሆን የዜጎችን መብት እንዳይጥሱ ትርጓሜያቸው ላይ በትኩረት አንዲታይ አስገንዝበዋል።

የዜጎችን በህግ ፊት እኩል የመሆን መብትን በተመለከተ ለተከሳሽና ለምስክሮች በሚሰጠው ከለላ  ላይ ትኩረት አንዲደረግም ሰብሳቢዋ አክለዋል። ።

በጠቅላይ አቃቢ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ የተሰጡት አስተያየቶች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው በረቂቅ ማሻሻያው ውስጥ ይታያሉ ብለዋል።

በተለይም አዲሱ አዋጅ  የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከሚጥሱ ድንጋጌዎች የፀዳ እንዲሆን አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል።

በቀጣይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዲስ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከህዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሙህራንና ሌሎች የሚመለከታችው አካላት ጋር ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።

 

በዚህም አዋጁ የበለጠ እንዲዳብር የሚያስችሉ ተጨማሪ ሀሳቦች እንደሚካተቱ ይጠበቃል ብለዋል።