ሶዴፓ አዲስ ዓርማ አጸደቀ

108
ጅግጅጋ ሰኔ 12 /2011 የሶማሊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ)ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ሰብሰባ አዲስ ዓርማ አጸደቀ። ማዕከላዊ ኮሚቴው በጅግጅጋ ከተማ ባደረገው ሰብሰባ ቀደም ሲል የነበረውን ዓርማ ይዘትና ቅርጽ ቀይሯል። ፓርቲው ዓርማውን የቀየረው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዓርማውን እንዲቀየር በሰጠው ውክልና መሠረት መሆኑን የማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ ለኢዜአ አስታውቀዋል። ዓርማው ፓርቲ የቆመላቸውን ዓላማዎች እንዲያንፀባርቅላቸው ተደርጎ መቀረጹንም አስረድተዋል። አዲሱ ዓርማ መደቡ ሰማያዊ በመሃል ግመል ሁለት ነጭ ቀለም ያላቸው መንገድ ምልክት የያዘ ሲሆን፣ በዙሪያው ደግሞ ሁለት መሥመሮች አሉት። በዚህም ሰማያዊው መደብ ሰላምን፣ግመሉ ደግሞ የክልሉን ሕዝብ አርብቶ አደርነት እንደሚወክሉ ኃላፊው አብራርተዋል። እንዲሁም ሁለቱ መሥመሮች የልማት፣የሰላምና የዴሞክራሲ ጎዳና እንደሚያመላክቱ ገልጸዋል። በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማን የሚወክሉ ቀላማት በዓርማው ተካትውበታል ብለዋል። ሶዴፓ 21ኛው የምስረታ በዓል በመጪው ሳምንት በጅግጅጋ ከተማ ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ኢንጂነር መሐመድ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም