የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ልማት እንዲስፋፋ ለግል ባለሃብቶች ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል ።

130
አዳማ  ሰኔ 12/2011 በሃገሪቱ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ልማት እንዲስፋፋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለግሉ ባለሃብት የተቀናጀ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሳሰበ። በኬሚካልናኮንስትራክሽንግብዓቶችኢንዱስትሪልማትኢንስቲትዩትአዘጋጅነት “ልዩትኩረትለሃገርውስጥአምራችኢንዱስትሪዎች” በሚልመርህየንቅናቄመድረክዛሬበአዳማከተማተጀምሯል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቅአየሁ እንዳሉት ሃገሪቱ በቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህ ግብ መሳካት ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የሃገሪቱን ጥሬ ዕቃ በስፋት የሚጠቀሙ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ አቅጣጫ በተለይ ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለፓኬጂንግና ለኮንስትራክሽን ግብዓቶች መጠናከርና ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የልማት ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ። "በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ውጤቶችን ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች፣ ለፍጆታና ለኮንስትራክሽን አገልግሎት እየተጠቀመች ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በእነዚህ ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶችን የበለጠ ለማስፋፋትና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት በኢንዱስትሪው ሴክተር የሃገር ውስጥ ባለሃብት በስፋት እንዲሳተፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ድጋፍ እንዲሰጡ ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ እየተረባረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ በበኩላቸው በኬሚካል ዘርፍ በተለይ በሳሙና፣ በማዳበሪያ፣ በፔትሮ ኬሚካል፣ በፐልፕና ወረቀት፣ በጎማና በፕላስቲክ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች በመጠን፣ በጥራትና በዋጋ የተወዳዳሪነት ዕድገት መመዝገቡን ገልጸዋል። በኮንስትራክሽን ግብአት ረገድም በሲሚንቶ፣ በሴራሚክ፣ በፈርኒቸር ፣ በዕብነበረድ ፣ በግራናይትና በቴራዞ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ምርቶችን በስፋት እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል። በዘርፉ ካጋጠሙ ተግዳራቶች መካከል የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና በክህሎት አቅም የፈጠረ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን አንስተዋል። በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት በዘርፉ 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል መመዝገቡን ኢንስቲትይቱ አስታውቋል። ከ2008 ዓ.ም ወዲህ በዘርፉ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከ26 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከክልልና ከፌዴራል መንግስት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም