ለታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ጥገና ተጠቃሚ ተቋማት እገዛ ማድረግ አለባቸው ተባለ

154

ሰኔ 12/2011በአማራ ክልል ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ለመጠገን እየገጠመ ያለውን የበጀት እጥረት ለመፍታት ከዘርፉ ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማት እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ ከቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ ዛሬ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የፈንዱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሺዋስ ደሳለኝ በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት በአማራ ክልል የሚገኙ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶች አንዱ የጉዳት መንስኤ የበጀት እጥረት ነው፡፡

ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠገን በዓመት ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም በተጨባጭ እየተመደበ ያለው ከ45 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለቅርስ ጥገናና ክብካቤ ሥራ የክልሉ መንግስት 42 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅሰው ይህም በዓመት ከሚያስፈልገው ግማሽ ያህሉን አይሸፍንም ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን ከጉዳትና ከጥፋት ለመታደግ የመንግስት ድጋፍ ብቻ በቂ እንዳልሆነና ከቱሪዝም ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማትና አካላት አቅማቸው በፈቀደ መጠን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ድጋፉ በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ጠቅሰው የፈንድ ጽህፈት ቤቱ መቋቋም ህብረሰቡን በማነቃነቅ ለቅርስ ጥገናና ክብካቤ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ድጋፉን በማሰባሰብ አደጋ ላይ የሚገኙ ቅርሶችን በመጠገን ለትውልድ የሚሻገሩበትን መንገድ የማማቻቸት ሥራ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

“ጽህፈት ቤቱ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል” ያሉት ኃላፊው ከቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች፣ ከቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ማህበራት፣ ቅርስን ከሚያስተዳድሩ አካላትና ከህብረተሰቡ ለቅርስ ጥገና የሚውል በጀት ለማሰባሰብ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛት አብዩ በበኩላቸው እንዳሉት የፈንዱ መቋቋም በክልሉ በጥገና በጀት እጥረት አደጋ ላይ የወደቁ ቅርሶችን በፍጥነት ጠግኖ ከአደጋ ስጋት ለማላቀቅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ቢሮው በጥገና እጦት ለአደጋ ስጋት የተጋለጡ ቅርሶችን በጥናት በመለየት ጥገና የሚካሄድባቸውን አሰራር ከፈንድ ጽህፈት ቤቱ ጋር በመቀናጀት እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡

“የፈንድ ጽህፈት ቤቱ መቋቋም በክልሉ በበጀት እጥረት ሳይጠገኑ ለጉዳት የተጋለጡ ቅርሶችን ለመታደግ” ያስችላል ያሉት የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላዕከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓአለም ናቸው፡፡

በጎንደር ከተማ የሚገኘው የጎሃ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ አጥናፉ በበኩላቸው” ቅርሶች ከሌሉ ቱሪስት የለም፤ የሆቴሎች ህልውና መሰረቱ ቱሪዝም በመሆኑ ለፈንዱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሆቴሉ ዝግጁ ነው” ብለዋል ፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በአማራ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትና ባለሀብቶች፣ የአስጎብኚ ማህበራት፣ የቅርስ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የወረዳ ፣ የዞንና የክልል የባህልና ቱሪዝም አመራሮች ተሳትፈዋል ፡፡

ር)