ለጤና መድህን ሽፋን ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች ከ949 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

121
ሰኔ 12/2011  የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት ከ949 ሚሊዮን ብር በላይ ለጤና ኢንሹራንስ ሽፋን የሚውል ገንዘብ ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች መሰብሰቡን ገለጸ። ተጠቃሚዎች በበኩላቸው የጤና ኢንሹራንስ አገልግሎት ሽፋን በማግኘታቸው በተለያዩ ጊዜያት ለመድኃኒትና ለምርመራ ሲያወጡት የነበረው ወጪ እንደቀነሰላቸውና የተሻለ ህክምና እያገኙ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጄንሲ የዕቅድና ጥናት ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ታየ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት ከ949 ሚሊዮን ብር በላይ ለጤና እንሹራንስ ሽፋን የሚውል ገንዘብ ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች ተሰብስቧል ። በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለጤና ኢንሹራንስ አገልግሎት ሽፋን የሚውል ገንዘብ ከነባርና አዲስ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ለመሰብሰብ ቢታቀድም ማሳካት የተቻለው 73 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል። "የጤናመድህን ሽፋን ስርዓቱን ውጤታማነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የፈንዱን የገንዘብ አሰባሰብ አቅም ይበልጥ ማጠናከር አለብን" ብለዋል። ለእዚህም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማዳበርና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ከማድረግ በተጨማሪ በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። "የመድን ዋስትናው ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ሥርዓቱን ከማሻሻል ጀምሮ በህብረተሰቡ ውስጥ ሰፊ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችል የዳሰሰ ጥናት በ50 ቀበሌዎች ተካሔዷል" ብለዋል አቶ ቢኒያም። በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር ቢቻልም አሁንም ካለው አቅም አንፃር የተፈለገውን ያህል መሄድ አለመቻሉን ተናግረዋል ። "በተመሳሳይ በታዳጊ ክልሎች በጅምር ላይ የሚገኘውን ፕሮግራም ውጤታማ በሆነ መንገድ አጠናክሮ ለማስቀጠል የጤና ሴክተርና የአስተዳደር አካላት የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል" ብለዋል። ለጤና መድህን አገልግሎት ውል የተገባባቸው የጤና ተቋማት እስከ ከፍተኛ ህክምና ድረስ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ከመድኃኒትና ከህክምና መሳሪያዎች ጋር ያሉ ክፍተቶችን በመፍታት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በወረዳው 10 ሺህ 300 የሚሆነኑ አባውራዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በምስራቅ ሸዋ ዞን የአደኣ ወረዳ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና ኢንሹራንስ ኤጄንሲ ኃላፊ አቶ አብዱ ሬድ ናቸው። በዘንድሮ ዓመት ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች  ለጤና ኢንሹራንስ ሽፋን ከተሰበሰበው 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ አገልግሎት ለሰጡት 7 ጤና ጣቢያዎችና አንድ ሆስፒታል  ፈሰስ መደረጉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በባንክ ሒሳብ መቀመጡን ጠቅሰው አግልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። በምስራቅ ሸዋ ዞን አደኣ ወረዳ የድሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አቶ ውብሸት ካሳሁን በበኩላቸው የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ስድስት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸዋል ። በዓመት 245 ብር እየከፈሉ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ውብሸት ከድሬ ጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቢሾፍቱ ሪፌራል ሆስፒታል ድረስ እሳቸውና ሰባት የቤተሰቦቻቸው አባላት አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። "በእስካሁኑ ሂደት በጤና ጣቢያውም ሆነ በቢሾፍቱ ሆስፒታል ከምርመራና ህክምና ጀምሮ እያገኘን ያለው አገልግሎት የተሻለ ነው" ያሉት አቶ ውብሸት መድኃኒቱን ከጤና ተቋማቱ ካላገኘን ውል ወደ ተገባላቸው የግል መድኃኒት ቤቶች በመሔድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ደስታ ተሾመ እንደተናገሩት ባለቤታቸውና እሳቸውን ጨምሮ ዘጠኝ የቤተሰብ አባላት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በጤና ተቋም ህፃን ልጃቸውን እያስከተቡ የነበሩት ወይዘሮ ደስታ ተሾመ በቢሾፍቱ ሆስፒታል ያለ ምንም ክፍያ የአባልነት መታወቂያ በማሳየት ብቻ እስከ ቀዶ ሕክምና ድረስ የአገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም