መንግስት የምጣኔ ኃብት አመራር ህግ አውጥቶ በመተግበር በዘርፉ ውስጥ ያለውን ሚና መወሰን አለበት - ምሁራን

65
ሰኔ 12/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የምጣኔ ኃብታዊ አመራር ህግ አውጥቶ በመተግበር በዘርፉ ውስጥ ያለውን ሚና መወሰንና የግል ዘርፉን ማበረታታት እንደሚገባው ምሁራን ገለፁ። መንግስት በዋነኝነት በግል ዘርፉ የሚመራ  ምጣኔ ኃብታዊ የልማት አቅጣጫን መከተል እንዳለባትም ነው ምሁራኑ ያስረዱት። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ምጣኔ ኃብታዊ ልማት በዋነኝነት የሚመራው በመንግስት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነው። የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ እንደሆነም ይነገራል። የግል ባለሃብቱ ሀገራዊ የምጣኔ ኃብት ተሳትፎ አለመጎልበት ደግሞ የመንግስት የልማት እንቅስቃሴ ለብክነት እንዲጋለጥ እያደረገው መሆኑን ምሁራኑ ገልፀዋል። ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ስትከተለው የቆየችው ልማታዊ መንግስት የተሰኘው የእድገት አቅጣጫ  ከፍተኛ የመንግስት ጣልቃ ገብነት የተስተዋለበት ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ሀገሪቱ እየተከተለችው የቆየችው ልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ አቅጣጫ የግል ዘርፉን ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን በመርህ ደረጃ የተቀበለ ቢሆንም በተግባር የሚስተዋለው ግን ሰፊ የመንግስት ጣልቃ ገብነት የተንፀባረቀበት መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም የግል ባለሃብቱ ጠንክሮ እንዳይወጣ ከማድረግ ባሻገር በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ  እንዳይኖረውና እንዲዳከም  አድርጎታል ሲሉም ይገልፃሉ። የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ልማት ጠንካራና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የግል ባለኃብቱ ሚና የጎላ ነው ያሉት ምሁሩ፤ መንግስት የምጣኔ ኃብታዊ አመራር ህግ አውጥቶ በመተግበር በዘርፉ ውስጥ የሚኖረውን ሚና መወሰንና የግል ዘርፉ እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል። በተለይም የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ኃብቱ ልማት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ። መንግስት በምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ፍትህን የማስፈን ተግባርን መከወንና በተለይ በረጅም ጊዜ ትርፍ የሚያስገኙ እንደትምህርት ያሉ ዘርፎች ላይ በትኩረት  ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት። የግል ባለሃብቱ የኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ለመሆን እንዲችልም ተወዳዳሪነቱን ማሳደግና በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን መከወን ይኖርበታልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ታዳጊ ሀገራት የግል ሴክተሩ በስልጣን ላይ በሚኖረው መንግስት ድጋፍ የተቋቋመ ነው ያሉት ዶክተር ብርሃኑ የነበረው መንግስት ላይ ለውጥ ሲመጣ የግል ዘርፉ ስለሚዳከም ወዳልተገባ ተግባራት እንደሚገባ ገልፀዋል። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት መንግስት መር ኢኮኖሚ ሀገሪቱ ስትከተል የነበረው የምጣኔ ኃብታዊ ልማት መንገድ መንግስት በመሰረተልማት ዝርጋታና በድህነት ቅነሳ ላይ በፈለገው መጠን መዋእለ ንዋይ እንዲያፈስ የሚያስችል ቢሆንም የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ ግን የሚያቀጭጭ ነው ያሉት ደግሞ የልማታዊ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ደረጄ ደጀኔ ናቸው። የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ አለመጎልበት ደግሞ የመንግስት የልማት እንቅስቃሴ ለብክነት የተጋለጠ እንዲሆን በማድረግ የሚፈጠረው ባለሃብትም ከዚሁ ብክነት የተገኘ እንዲሆን እንደሚያደርግ አብራርተዋል። ዜጎችም የመሰረተልማት አውታሩ ተጠቃሚ ቢሆንም የኢኮኖሚ ባለቤተነቱ እየደከመ እንዲመጣ  የሚያደርግ መሆኑን በመግለፅ። ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ አብዛኛውን  መንግስት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለግል ዘርፉ እየለቀቀ  መሄደ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም