ፈረንሳይ የኢትዮ -ኤርትራን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች - የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

45
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በምታደርገው እንቅስቃሴ ፈረንሳይ ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ይቬስ ሊ ድሪያን ገለጹ። የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፈረንሳይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ይቬስ ሊ ድሪያንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፣ "የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው የሰላም እንቅስቃሴና የኢኮኖያዊ ማሻሻያ ተስፋ ሰጭ ነው"። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተቋርጦ የነበረው ግንኙነትም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል "ፈረንሳይ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ታደርጋለች" ብለዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፈረንሳይ ቋሚ፣  ኢትዮጵያ ደግሞ ተለዋጭ የጸጠታው ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሰላማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። ከሰላም ድርድሩ ባለፈ በመንግስት ስር በነበሩ የልማት ድርጅቶች የግል ባለሃብቱ አክሲዮን በመግዛት እንዲሳተፍ መደረጉ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል። ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንዲጎለብትም ጥረት “እናደርጋለን” ብለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው "የአገሪቱን ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እድገት ዘላቂ ለማድረግ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተቀባይነት ያላቸው ናቸው" ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም