ሊገነቡ የታሰቡ ሁለት የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ምዕራፍ የጨረታ ሂደት ተጠናቋል

68
ሰኔ 12/2011 በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ለመስራት ከታሰቡት ስምንት የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የሁለቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የጨረታ ሂደት መጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። በመንግስትና በግል አጋርነት ስለሚሰሩ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ኢዜአ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰን አነጋግሯል። የኢትዮጵያ የመንግስትና የግል አጋርነት ፅህፈት ቤት በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በሁለቱ አካላት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ማጽደቁ የሚታወስ ነው። በመንግስትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ የሚሰሩ 17 ፕሮጀክቶች እንደተለዩና ከነዚህም ውስጥ 14ቱ በኢነርጂ ዘርፍ የተቀሩት ሶስቱ ደግሞ በትራንስፖርት ዘርፍ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። ከነዚህ መካከል 8ቱ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ በአፋር ክልል ጋድና በሶማሌ ክልል ዲቼቶ የሚሰሩት የሁለቱ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ምዕራፍ የጨረታ ሂደት አልቋል። ከዚህ በኋላ የቴክኒክና የፋይናንስ ፕሮፖዛል እ.አ.አ ሰኔ ወር 2019 መጨረሻ ድረስ እንደሚያቀርቡ ዶክተር ተሾመ ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹ የመተማ፣ መቐለ፣ ሁርሶ፣ ዌራንሶ፣ ወለንጪቲና ሁመራ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ድርጅቶች በቀረበው ጥሪ መሰረት ከ85 በላይ ድርጅቶች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል። በቀጣይም ከሰባት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተወጣጥቶ የተቋቋመው ቦርድ ባወጣው መስፈርት መሰረት ለጨረታ ብቁ የሆኑ ድርጅቶች ይመረጣሉ ብለዋል። ስምንቱ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 1000 ሺህ ሜጋ ዋት የሚደረስ የኤሌትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸውና እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ ሊደረግባቸው እንደሚችልም ጠቁመዋል። በመንግስትና በግል አጋርነት የሚገኙ ቀሪ ፕሮጀክቶች በጊዜ ሂደት ድርጅቶችን በመመዝገብ ወደ ጨረታ እንደሚገቡም አመልክተዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ የግሉ ዘርፍ በሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ የተጀመረው ስራ የዘርፉን እውቀት ፋይናንስና አቅም ለመጠቀም እንዲሁም ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ያግዛል። መንግስትና የግሉ ዘርፍ በጋራ መስራት መጀመራቸው በፕሮጀክት ግንቦታዎች ላይ የሚኖሩ ችግሮች እና ፈተናዎች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው። በቀጣይም መንግስት እና የግሉ ዘርፍ የሚሰሩባቸው ፕሮጀክቶች እየተለዩ ወደ ስራ ይገባሉ ነው ያሉት። በትራንስፖርት ዘርፉ የአዳማ አዋሽ 125 ኪሎ ሜትር የፍጥነት  መንገድ በ440 ሚሊየን ዶላር፣ አዋሽ ሚኤሶ 72 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ በ230 ሚሊየን ዶላር እና ከሚኤሶ ድሬደዋ 160 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ የተለዩት ፕሮጀክቶች ናቸው። የዓለም ባንክ የኢነርጂ ባለሙያ ሚስ ቺያራ ሮጌት መንግስት የግሉ ዘርፍ በሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው በተለይም የህግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት አንጻር የተሻሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። በተለያዩ ዘርፎች ላይ መንግስት ጠንካራ ግምግማ በማድረግ የግሉ ዘርፍ በታዳሽ ሃይል አማራጮች ተሳትፎ ላይ ያለውን ምቹ አጋጣሚና ፈተናዎችንም መለየቱንም ገልጸዋል። መንግስት የኢነርጂውን ዘርፍ ለግል ባለሃብቱ ክፍት ለማድረግ ብዙ ጊዜ ቢወስድም የወሰዳቸው እርምጃዎችና ያከናወናቸው ስራዎች መልካም ጅምር ነው ብለዋል። የዓለም ባንክ የመንግስትና የግል አጋርነት የሃይል ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በኤሌትሪክ ሃይል በተለይም በጸሐይ ሃይል በሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በቀጣይም የዓለም ባንክ መሰል ድጋፎችን ለኢትዮጵያ የሃይል ዘርፍ ማድረግ እንደሚቀጥል ሚስ ቺያራ አረጋግጠዋል። በመንግስትና በግል አጋርነት ለተለዩት 17 ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገምቷል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም