በአፍሪካ ስደትና መፈናቀልን ለማስቆም መሪዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል....የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር

123
ሰኔ 12/2011 በአፍሪካ ስደትና መፈናቀልን ለማስቆም መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አስገነዘቡ ። የዓለም ስደተኞች ቀን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 65 ሺህ ስደተኞች በሚገኙበት ጾሬ የስደተኞች ካፕ ትናንት ተከብሯል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በተወካያቸው የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች  ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት በአፍሪካ አሁንም ዜጎች ከአገራቸው እየተሰደዱና ከመኖሪያ አካባቢያቸው እየተፈናቀሉ ነው። የእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ለስደቱም ሆነ ለመፈናቀሉ ምክንያት መሆናቸውን የገለጹት  ሊቀመንበሩ በእዚህም ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዋነኛ ተጎጂ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የአፍሪካ አገራት መሪዎች አሁንም የጎላ ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ  እንደሚገባ ሊቀመንበሩ በተወካያቸው አማካኝነት አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ያፀደቀችው ህግ የስደተኞችን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስጠብቅና በስደተኞች ጉዳይ  ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ እንደሚያደርጋት ጠቅሰዋል። በሀገራቸው ስደተኞችን በመንከባከብ ላደረጉት አስተዋጽኦ “የአፍሪካ ሕብረት የ2019 የስደተኞችና ከአካባቢያቸው ተፈናቃዮች ሻምፓዮን” የሚል ክብር የተሰጣቸው የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ አቢያንግ ኑዌማ ምባሶጎ በበኩላቸው በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ያዘችው ኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ የሆኑ ስደተኞችን ማስጠለሏን አድንቀዋል። ይህን በጎ ተግባር ለመደገፍም በጾሬ ስድተኞች ካፕ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል 50 ሺህ ዶላር በመንግስታቸው ስም ድጋፍ ሰጥተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ኃይለማሪያም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለስደተኞች በምታደግረው  እንክብካቤ ዘንድሮ ከአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብት ሽልማት ማግኘቷን ተናግረዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚስተር ጆርጅ  ኦኮዝ-ኦቦ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ለስደተኞች ጉዳይ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠክር አስታውቀዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕስ መስተዳደር ተወካይ አቶ ቶማስ ኩዊ በበኩላቸው አሁንም ወደ ክልሉ  የአጎራባች አገራት ስደተኞች በመግባት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቻችለው እየኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የዓለም ስደተኞች ቀን ሲከበር የተገኙት ከፍተኛ አመራሮች በካምፑ የችግኝ ተከላ ያካሄዱ ሲሆን የስደተኞችን መኖሪያ አካባቢንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም