አራት ጊዜ የተራዘመው የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቀቀ

59
ሰኔ 11/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራት ጊዜ የተራዘመው 27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ። በዛሬው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ይዞ በመጫወት ወደ ግብ ለመቅረብ የሞከረ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታ በመልሶ ማጥቃትና በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ግብ ለመቅረብ ሞክሯል። በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩ ቢሆንም በግብ ጠባቂዎች ጥረት ከሽፈዋል። በዕለቱ ከጨዋታ በፊትና በጨዋታ ሰዓት የጣለው ዝናብ ሜዳውን ለጨዋታ እንዳይመች በማድረጉ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ለመቆጣጠር ሲቸገሩ ነበር። የመቐለ 70 እንደርታ ሁለት ተጫዋቾች በጨዋታ ላይ በፈጸሙት ጥፋት የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ በእለቱ የመሃል ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ሰጥተዋል። ጨዋታው ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አንድ ነጥብ ያገኘው መቐለ 70 እንደርታ ከመሪው ፋሲል ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት አጥብቧል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች የስታዲየሙን መቀመጫ ወንበር ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ሲወራወሩ በጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ሊቆም ችሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከተማ በ52 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ መቐለ 70 እንደርታ በ50 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ሲዳማ ቡና በ49 ነጥብ ሶስተኛ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም