ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ትራንስፎርመሮች ለኢንዱስትሪዎች ፈተና ሆነዋል

54
ሰኔ 11/2011 የኢትዮጵያን የኃይል መቆራረጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችና  ትራንስፎርመሮችን መቀየር እንደሚገባ ጥናት አመለከተ። በኢትዮጵያ የቢዝነስ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች በተደረገ ጥናት አብዛኞቹ ተቋማት ለኪሳራ የሚጋለጡት በኃይል መቆራረጥ እንድሆነ ተገልጿል። እነዚህ ተቋማት በኃይል መቆራረጥ ምክንያት በ2010 ዓም ብቻ 95 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር አጥተዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኤ.ቢ.ዲ አማካሪ ጋር በመተባበር ያስጠናው ጥናት ውጤት   እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በዓመት ለበርካታ ጊዜ መብራት የሚቆራረጥባት አገር ናት። የኤ.ቢ.ዲ አማካሪ ዋና ስራ አስኪያጅ ባቀረቡት የጥናት ግኝት፤ በ2010 ዓመት በአዲስ አበባ ብቻ 25 ሺህ 492 ጊዜ ለ19 ሺህ 937 ሰዓት ጠፍቷል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2016 በእንግሊዝ በዓመት 80 ደቂቃ፣ ስዊዘርላንድ በበረዶ ግግርና በከፍተኛ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆና በዓመት ለ30 ደቂቃ ብቻ ነው የጠፋባቸው ይላሉ። የጥናቱ ግኝት በኢትዮጵያ የንግድ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች በከፋ የኃይል እጥረት ውስጥ እንዳሉ መሳያ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከአራት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ሃይል ብታመነጭም አገልግሎት ላይ የዋለው ከሁለት ሺህ 550 ሜጋ ዋት አይበልጥም ብለዋል። በዚህም ኢንዱስትሪዎች ለኪሳራ ተዳርገዋል፤ የምርታቸው ጥራትና መጠን ቀንሷል፤ በዘርፉ የሚፈጠረውም የስራ እድል ቀንሷል። በተጨማሪም የማሽን ብልሽት፣ የንብረት ውድመት፣ የተቀጣሪዎች ማህበራዊ ህይወት መናጋት እንዲሁም አገራዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈጥራል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማርጀት፣ የኃልይ መቆጣጠሪያ /ትራንስፎርመሮች/ አቅም ውስንነት ይታይባቸዋል ነው ያሉት። ከዚህም ባለፈ ቀልጣፋ የቅሬታና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት አለመኖር፣ ከልክ ያለፈ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ ኋላቀር የጥገና አገልግሎት፣ ደካማ የአስተዳደር ስርዓት የችግሮቹ መንስኤዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም መንግስት ችግሩን በውል ተገንዝቦ ትራንስፎርመሮችና ያረጁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መቀየር ይኖርበታል ብለዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭቱን ለመቆጣጠርና ለመከታተል እንዲያመች ያልተማከለ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም