ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ነው

137

ሰኔ 11/2011 “ናትና ስፖርት” በሚል ስያሜ በየዓመቱ የሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በመቀሌ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የውድድሩ አዘጋጅ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማሪያም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ውድድሩ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ታዳጊ ህጻናት በሚሳተፉበት ይጀመራል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዴሃቂ ግቢ በሚገኘው ስታዲየም በሚጀመረው በእዚህ ውድድር በርካታ ህጻናት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል።

በማግስቱም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ አዋቂዎች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመቀሌ ከተማ የሚካሄድ መሆኑን አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገልጿል።

አዋቂዎች በሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር አትሌት ሀጎስ ገብረመስቀልን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ለሚወጡም ከ60 ሺህ እስከ 2ሺህ 500 ብር ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

በየዓመቱ ውድድሩን ማካሄድ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያግዝ ከመሆኑ በተጨማሪ የስፖርት ቱሪዝምን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል።

“የጎዳና ላይ የስፖርት ውድድር ከተማዋን ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ አለው” ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማይ ተስፋይ ናቸው።

የስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዳ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።