ብሔር ተኮር ፖለቲካ የዜጎች አብሮ የመኖር እሴት እንዲሸረሸር አድርጎታል - የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ

109
ሰኔ 11/2011 በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች አግባብ ባልሆነ መልኩ የተሰበከው ብሄር ተኮር ፖለቲካ የአገሪቱ ህዝቦች የቆየ አብሮ የመኖር እሴት እንዲሸረሸር አድርጓል ሲሉ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ገለፁ። ኢትዮጵያ የራሳቸው ባህል፣ ሐይማኖት፣ ማንነት፣ ቋንቋና ታሪክን ጨምሮ አያሌ ድንቅ መገለጫዎች ያሏቸው ከ80 በላይ ልዩ ልዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት ምድር ናት። በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ ግን  ዜጎቿ እጅግ የጎለበተ አብሮ የመኖር፣ ችግርን በጋራ የመፍታት፣ የመከባበር፣ የመረዳዳትና የመቻቻል እሴቶች ባለቤትም ናቸው። በዚህም የተነሳ አገሪቱና ህዝቦቿ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር በምሳሌነት ሲነሱ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ አብሮ የመኖር፣ የመከባበርና መቻቻል ወርቃማ እሴቶች አደጋ ላይ መውደቃቸውን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች በስፋት መታየት መጀመራቸውን ብዙዎች ይገልፃሉ። በተለይም ከብሄርና ማንነት ጋር በተያያዘ የሚታየው መገፋፋት፣  አንዱ በሌላው ላይ የሚፈጽመው እስከ ህይወት ማሳጣት የደረሰ ጥቃት እኒህ እሴቶች እየተሸረሸሩ ስለመሆናቸው ዓብይ ማሳያ  መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር አበጀ ብርሃኑ ይናገራሉ። የብሄር ግጭት፤ የዜጎች መፈናቀልና ለማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግር መጋለጥ ምክንያቱ የህዝቦች አብሮ የመኖርና መቻቻል እሴቶች እየጠፋ መምጣት መሆኑንም ያስገነዝባሉ። ምንም እንኳ ለእሴቶቹ መዳከም የምጣኔ ኃብታዊ ድህነትን አንዱ ምክንያት አድርገው የሚያነሱ ጥቂቶች ያሉ ቢሆንም እንደ ዶክተር አበጀ ግን ከፖለቲካ ፍላጎት ጋር የተያያዙ የተዛቡ አመለካከቶች ለእሴቶቹ አደጋ ላይ መውደቅ እንደምክንያት ይገለጻሉ። በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደአሸን መብዛትና እነርሱም በየፊናቸው የሚያራምዱት ልክ ያልሆነ ብሔር ተኮር ፖለቲካ የብሄር ብሄረሰቦችን  አብሮ የመኖር የቆየ እሴት እየሸረሸሩት መሆናቸውን  የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር አበጀ ተናግረዋል። በተለይ ወጣቱ  ከህጻንነቱ ጀምሮ እየሰማ ያደገው ብሄርን ብቻ መሰረት ባደረገውና በአንድነትና በጋራ ከመኖር ይልቅ በመለያየት ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ ያለፉት ዓመታት ፖለቲካ አውድ ሰለባ ሆኗል ብለዋል ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ትርፍ ያገኙባቸው "ያንተ ብሔር ከእኔ ይበልጣል" የሚለው አፍራሽ መልዕክት እሴቶቹ እንዲሸረሸሪ እያደረገ መሆኑንም  ዶክተር አበጀ ተናግረዋል። አገሪቱ ያላትን እሴት እንዳታጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን ከብሄር በማጋጫት ከሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው ይላሉ ዶክተር አበጀ። የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግስትና ታዋቂ ግለሰቦች ወላጆች ለአዲሱ ትውልድ የመቻቻልና የመከባባር ባህልን የማስረፅ ቁልፍ ኃላፊነት አለባቸው ብላዋል። በኢትዮጵያ አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸርና ለግጭቶች መበራከት ‘’የኔ ከሁሉም ይበልጣል’’ የሚለው ዘመን አመጣሽ የተዛባ አስተሳሰብ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የትነበርሽ ንጉሴ ናቸው። "ትውልዱ  አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶችን  ወደ ጎን እንዲተው ራስ ወዳድነት ያጠቃው እንዲሆን መንስኤ እዚሁ አገር ያሳደግናቸው አሉታዊ አመለካከቶች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል ወይዘሮ የትነበርሽ። በቀጣይ የራሱን ድርሻ የሚያውቅና የሰው ድርሻ የሚያከብር ትውልድ የመፍጠሩ ስራ ከወላጅ ጀምሮ የሁሉም ሰዎች ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያሳሰቡት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም