በልማት ለተወሰደብን ነባር ይዞታ ተገቢ ካሳና ምትክ መሬት አላገኘንም.... በወላይታ ዞን አርሶ አደሮች

62
ሶዶ ሰኔ 1/2010 ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ለተወሰደባቸው ነባር ይዞታ ተገቢ ካሳና ምትክ መሬት አለማግኘታቸውን በወላይታ ዞን በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የዳዳ ካረ ቀበሌ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው እየተካሄደ ላለው የቴክኒክና ሙያ ማልጠኛ ተቋም ከ15 ሄክታር በላይ መሬት ላይ አርሶአደሮች ይዞታቸውን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ አርሶአደሮቹ እንደሚሉት ለነባር ይዞታቸው ተገቢው ካሳና ምትክ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቢነገራቸውም እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡ በዚህም "ለችግር ተጋልጠናል" ሲሉ ነው ለኢዜአ ቅሬታቸውን የገለጹት፡፡ ከ1 ነጥብ 5 በላይ ሄክታር መሬት ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረቱ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ነባር የመሬት ይዞታቸውን ለልማት እንዲውል መፍቀዳቸውን የተናገሩት የቀበሌው አርሶ አደር ኢሳያስ ባልቻ ናቸው፡፡ በቂ ካሳና ተለዋጭ የእርሻ መሬት እንደሚሰጣቸው ከወረዳው ቢነገራቸውም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንና በተደጋጋሚ ተመላልሰው ቢጠይቁም መፍትሄ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ የእርሻ ቦታቸውን አልምተው መጠቀም በሚችሉበት ወቅት ያለስራ ተቀምጠው የተቋሙ ግንባታ መከናወኑ ሚዛናዊነት የሚጎድለው በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አርሶአደር ታምራት ኡፋይሳ ለልማቱ ሲባል መሬታቸው ቢወሰድም የመንግስት አካላት የገቡትን ቃል ባለማክበራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ "አካባቢው የመንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ያልተሟላለትና  የከተማ ፕላን ያልደረሰበት መሆኑ በራሱ የትምህርት ተቋሙ ያለዕቅድ የተሰራ ስለመሆኑ ያሳያል" ብለዋል፡፡ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 2 ነጥብ 5 ሄክታር የእርሻ መሬታቸው ሙሉ በሙሉ በመወሰዱ ምክንያት ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንደከበዳቸው የገለጹት አርሶአደሩ "ችግራችንን ሰምቶ መልስ የሚሰጠን አካል አጥተናል" ብለዋል፡፡ በወረዳው የበሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬሁን ግርማ በበኩላቸው ቀደም ሲል በቀበሌ 04 ዳዳ ካረ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከ15 ከሚበልጡ አርሶ አደሮች የእርሻ መሬታቸው ለልማት መወሰዱን አምነዋል፡፡ አከባቢው በከተማ ማስፋፊያ ፕላኑ መሰረት ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ የተቀመጠ በመሆኑ ግንባታው መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡ በቦታው ላይ የነበሩ አርሶአደሮች ባለይዞታ በመሆናቸው ተገቢ ካሳና ምትክ መሬት ለማቅረብ ስምምነት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው ፕላን ላይ ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች በመኖራቸው ምክንያት መዘግየቱንና በአሁኑ ወቅት ከዞኑ ጋር በመነጋገር  የተሰራው የማስተካከያ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ "ለነባር ባለይዞታዎችና ልጆቻቸው ህጉ በሚፈቅፈው መሰረት ምትክ ቦታና ካሳ ለመክፈል አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በሚቀጥሉት ሃያ ቀናት ችግሩ በአግባቡ ይፈታል" ብለዋል፡፡ በወላይታ ዞን የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ጸሐይ ገብረሚካኤል በበኩላቸው "የዳዳ ካረ አርሶ አደሮች ቅሬታ ትክክል ነው" ብለዋል፡፡ በሰዓቱ ምላሽ ለመስጠት የከተማ ፕላን ለውጥ ከማስፈለጉ በተጨማሪ የበጀት እጥረት ለክፍተቱ መነሻ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ምትክ ቦታ በሚሰጥበት አካባቢ ውሃ፣ መብራትና መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች የማሟላት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠውም አመልክተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም