በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ በኩባንያው ስህተት የተፈጠረ ነው---የቦይንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙለንበርግ

64
ሰኔ 11/2011 የቦይንግ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙለንበርግ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ በኩባንያው ስህተት የተፈጠረ በመሆኑ ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ ጠይቀዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው ትናንት ፓሪስ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ይቅርታ ጠይቀዋል። ከአደጋው በኋላ ከባድ ፈተና ላይ የወደቀው ቦይንግ ኩባንያ በመላው አለም የሚገኙ ተመሳሳይ ምርቶቹን ከበረራ ማገዱ ይታወሳል። “ህይወታቸውን ላጡት ሰዎች ከልባችን እናዝናለን” በማለት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዴኒስ ሙለንበርግ ፈረንሳይ ላይ በተከናወነው የፓሪስ ኤር ሾው ላይ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አደጋውን ተከትሎ ለተጉላሉት ተጓዞችና አየር መንገዶች ይቅርታቸውን አቅርበዋል። “ይህ ለእኛ ወሳኙ ጊዜ ነው ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ አደጋ እንደማይከሰት እርግጠኛ የምንሆንበትም ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢንዶኔዥያው ላየን ኤይር 737 ማክስ አውሮፕላን በደረሰባቸው አደጋ የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። የተፈጠረውን አደጋ በተመለከተ ምርመራው ባይጠናቀቅም ዋና ስራ አስፈጻሚው ዴኒስ ሙለንበርግ የአውሮፕላኑ አውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ለአደጋው አስተዋጽኦ እንደነበረው አምነዋል። መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሩ የአውሮፕላኑን አፍንጫ ወደ ታች በመድፈቅ ለአደጋው መከሰት ምክንያት መሆኑ ይታመናል። የአውሮፕላን አብራሪዎቹም በድጋሚ በረራውን ለመቆጣጠር እንዳልቻሉም በባለሙያዎች ተገልጿል። በፓሪስ ኤር ሾው ላይ በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዴኒስ ሙለንበርግ የቦይንግ ኢንጂነሮች ፓይለቶቹን የሚያስጠነቅቀው ሶፍትዌር ችግር እንዳለበት እኤአ በ2017 እንደደረሱበት ተናግረዋል። ነገር ግን ችግሩን በተመለከተ ከአለም አቀፍ የአቪየሽን ባለስልጣናት ጋር በግልጽ አለመነጋገሩ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ እንደነበርም በይቅርታ መልክ ገልጸዋል። አደጋውን ተከትሎ የታገዱት አውሮፕላኖቹ መቼ ወደ በረራ እንደሚመለሱ በግልጽ የተቆረጠ ቀን አለመኖሩንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም