የጤና መድህን ኢንሹራንስ ስርዓት የተፈለገውን ያክል ውጤታማ አልሆነም

114
ሰኔ 11/2011 የጤና መድህን ኢንሹራንስ ስርዓት የተፈለገውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኤጀንሲ ገለጸ። በሀገሪቷ ካሉት ከ1ሺህ በላይ የገጠር ወረዳዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት መስጠት የጀመሩት 427 ወረዳዎች ብቻ ናቸው ተብሏል ። ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውን ግምገማ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚዛን ኪሮስ እንደገለጹት የጤና መድህን ኢንሹራንስ ስርዓት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። በገጠር ከሚኖረውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል 80 በመቶ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተቀምጦ ወደሥራ ቢገባም ማሳካት የተቻለው በአማካይ 43 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል ። ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ "በተጨባጭ ተደራሽ ማድረግ የተቻለው 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን ብቻ ነው" ብለዋል ። የጤና መድህን ስርዓቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አለመዳበርና  በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት ለዕቅዱ አለመሳካት በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። "በዲሱ የበጀት ዓመት የተቀናጀ የጤና መድህን ኢንሹራንስ ንቅናቄ በመፍጠር ዕቅዱን ለማሳካት ከወዲሁ የዝግጅትና የሪፎርም ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ነው" ብለዋል ። ከእዚህ በተጨማሪ በጤና ተቋማት ከአገልግሎት ጥራት ፣ በመድኃኒትና በህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት ከመንግስትና ከግል የጤና ሴክተር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ሚዛን ጠቁመዋል ። የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ያቀረቡት የኤጀንሲው የዕቅድና ጥናት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ታዬ በበኩላቸው የመንግስት የጤና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ በመድኃኒት አቅርቦት፣ በአቅም ግንባታ፣ በዋጋ ተመንና በክፍያ ፖሊሲ ላይ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። "ፈጣን የጤና አገልግሎት ስርዓት እንዲኖር እየሰራን እንገኛለን" ያሉት አቶ ቢኒያም በ444 የጤና ተቋማት ላይ 2 ሺህ 120 የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች ቀርበው 1ሺህ 904 ቱ መፈታታቸውን ተናግረዋል። በኤጀንሲውም ሆነ በጤና ተቋማት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከአገልግሎት ጥራት፣ ከመድኃኒትና ከአቅም ግንባታ ስራዎች ጋር በተያያዘ በ1ሺህ 575 የጤና ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት ተካሔዶ የጥናቱ ግኝት ለመንግስትና ለባለድርሻ አካላት መቅረቡን አስረድተዋል። "በዘንድሮ ዓመት ውል ለተገባላቸው ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ለሰጡት አገልግሎት ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ኤጀንሲው ፈሰስ አድርጓል" ብለዋል። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከኤጀንሲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከጤናው ሴክተር የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም