በሳዑዲ ዓረቢያ በህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ የሆነው ታዳጊ መሀመድ አብዱልአዚዝ አዲስ አበባ ገባ

80
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በሳዑዲ ዓረቢያ ሆስፒታል ውስጥ በተፈጸመ የህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ የሆነው ታዳጊ መሀመድ አብዱልአዚዝ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል። ታዳጊው መሀመድ አብዱልአዚዝ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የህክምና ባለሙያዎች አቀባበል አድርገውለታል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የታዳጊውን እናት ወይዘሮ ሀሊማ ሙዘይል አግኝተው አበረታተዋል፤ አፅናንተዋል። የታዳጊውን እናት ወይዘሮ ሀሊማ ሙዘይል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር በመነጋገር የልጃቸው ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረጋቸው ምስጋና ችረዋል።  የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ታዳጊ መሀመድ አብዱልአዚዝ ተቀብሎ አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፆ ነበር። በመሆኑም የአልጋ ቁራኛ የሆነውን ታዳጊ መሀመድ አብዱልአዚዝ  ከቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ  በተዘጋጀው አምቡላንስ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ወደ ተዘጋጀለት የህክምና እርዳታ መስጫ ክፍል አቅንቷል። ታዳጊው በሆስፒታሉ በሚኖረው ቆይታ በተሟላ የህክምና ቡድን በተቀናጀና በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የህክምና እርዳታ እንደሚሰጠው የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም