ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የዕድርን አቅምና እሴቶች መጠቀም አስፈላጊ ነው

245
ሰኔ 10/2011የዕድርን አቅምና አገራዊ እሴቶቹን በመጠቀም ማህበራዊ ችግሮች መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ። ለአገሪቱ  ብሎም በመዲናዋ ለሚገኙ ክፍለ ከተሞች የጤና ስጋት የሆነውን የአተት በሽታ፣ የ”HIV/ኤድስ”፣ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል እንዲሁም የትንባሆ ጭስ መከላከልን አስመልክቶ ነው ጥሪው የቀረበው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከከተማዋ የእድሮች ምክር ቤት ዓመታዊ የልማትና የሰላም ንቅናቄ አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች 2 ሺ 500 የእድር አባላትና ተወካዮችን አወያይቷል። የቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲኖርና ሁሉም ቤተሰብ ጤናው እንዲጠበቅ ብሎም በክፍለ ከተሞቻችን እየታየ ያለው የአተት በሽታ እንዳይዛመት ዕድሮች በጤናው ዘርፍም በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ወይዘሮ አለምፀሐይ አያይዘውም ሁሉንም የእድር አባላትና ተወካዮቹ ህብረተሰቡ ለምግብነት በሚጠቀማቸው ባዕድ ነገሮችን የሚቀላቀሉና ሞራል የጎደላቸው አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማጋለጥ ህብረተሰቡን ከችግር እንዲጠብቁም ነው ያሳሰቡት። "የእድሮችን ጥያቄ መመለስ ማህበራዊ ችግሮችን መፈታት ነው" ያሉት የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ደግሞ፤ እድሮቹ ወደ ህዝቡ ሆነው እያወያዩና በአገራዊ እሴትና አደረጃጀት ወደ ለማህበረሰቡ መፍትሔ ይሰጣሉ ብለዋል። ስለሆነም እድሮች አገር አቀፍ ልማታዊ አንጓና መሠረት በመሆናቸው ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው መፍትሔ ስለሚሰጡ የማህበራዊ ችግሮች መፍትሔ ሰጭ አምባሳደሮች መሆን እንዳለባቸውም አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል። በመድረኩም እድሮቹ በሀዘን፣ በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኙ ነዋሪዎችንና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ከሚያደርጉት ማህበራዊ ድጋፍ ጎን ለጎን ትውልድ መራዥ መጤ ባህሎችን በመከላከልም እንዲደግሙት ጥያቄ ቀርቧል። ዕድር ሐይማኖት፣ ፆታ፣ ዘር የማይለይ፤ ሁሉንም ዜጎች አቃፊ አገራዊ እሴት መሆኑንምለወደፊቱ አገራችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ካሰበቻቸው ቅርሶች አንዱ ነውም ተብሏል። በዘህም ዕድር በቀጠና ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም በመሆኑ ወደፊትም ቢሮው የራሱ አደረጃጀት፣ መዋቅርና ወጥ መመሪያ  እየሰራ ነውም ተብሏል። ከተለመዱ የእድር ተግባራት በተጨማሪ በትምህርት እና በኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ግዴታቸውን ለተወጡ እድሮች የምስጋናና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም