በደራሼ ወረዳ 305 ሄክታር መሬት አዝመራ በጎርፍ ወደመ

163

ዓርባ ምንጭ ሰኔ 10 / 2011  በደቡብ ክልል ደራሼ ወረዳ ጎርፍ በ305 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ አዝመራ አወደመ።

አደጋው በማሳ ላይ የነበረ የበቆሎና የማሽላ አዝመራ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን የወረዳው አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ግርማ ዳቲካ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ልዩ ስሙ አዋሳ በተባለው ስፍራ በደረሰው አደጋ 182 አርሶ አደሮች ማሳ ጉዳት እንደደረሰበት አስረድተዋል።

አደጋው ለስምንት ተከታታይ ቀናት በጣለው ዝናብ ሳቢያ በተፈጠረ ጎርፍና አቅጣጫ በሳተ ወንዝ መከሰቱን ባለሙያው አብራርተዋል።

በአደጋው አዝመራቸው የተጎዳባቸው አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ከደቡብ ክልል አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኮሚሽን ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም አስረድተዋል።

አርሶ አደር ጣኒዛ ጨነቀ በሰጡት አስተያየት በአደጋው አራት የእርሻ በሬዎች በጎርፍ እንደተወሰዱባቸውና በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል እንደወደመባቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የዋይቤ ቀበሌ አርሶ አደር ማህተመች መካሻ በበኩላቸው በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የበቆሎ አዝመራቸው ከጥቅም ውጭ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

በአደጋው ለደረሰባቸው ጉዳት መንግሥት ማካካሻ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።