ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተስቧል

74
ሰኔ 10/2011 ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቡን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። 13ኛው ዙር የኢንቨስትመንት  የጋረ የምክክር መድረክ የክልልና የፌዴራል የኢንቨስትመንት አካላት በተገኙበት በአፋር ክልል ሰመራ ተካሂዷል። በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የኢንቨስትመንት ግብ የወጪ ንግድን  ማሳደግ፣ የስራ ዕድል መፍጠርና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን እድገት ማፋጠንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ያለመ ነው። በኮሚሽኑ የዕቅድና ፖሊስ ጥናትና ስትራቴጂ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ተድላ ባቀረቡት ሪፖርት በ2007 ዓ.ም 2 ነጥብ 2 እንደዚሁም በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ደግሞ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ተስቧል። ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተደረገ ጥረት የኤግል ሂልስ፣ የቮልስ ዋገንና ሲመለስን የተሰኙ ግዙፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መደረጉ ተገልጿል። በተግባር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የተቻለው ግን 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሆኑ ተመልክቷል። በኢንቨስትመንት መስክ ግቦችን ለማሳካትም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፤ በ2009 ወደ ስራ የተገባውን የአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ አሁን ላይ ዘጠኙ ወደ ስራ ገብተዋል። እስካሁን በዘጠኙ የኢንዱሰትሪ ፓርኮች 70 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን ባለፉት  ዘጠኝ  ወራትም ከዘጠኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጭ ንግድ 103 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱም ተገልጻል። በሌላ በኩል በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በኩል የዕቅዱን 62 በመቶ በማከናወን 215 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን በሪፖርቱ ተመልክቷል። አጠቃላይ የኤክስፖርት አፈጻጸሙ ግን አንደ አገር በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ በኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ ማነቆዎቸን መፍታት አንደሚገባ ነው የተገለጸው። በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬና የፋይናንስ እጥረት፣ የመሰረተ ልማትና ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ያጋጠሙ ማነቆዎች ናቸው ተብሏል። በተለይም በአገሪቷ የነበረው አለመረጋጋት ፕሮጀቶች ላይ ያሳደረ ችግር ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው፤ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ ለቀው እንዳይወጡ የተሰራው ስራ አበረታች እንደነበር አብራርተዋል። በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ከወሰዱት ፈቃድ ውጭ ለሌላ ዓላማ እንደሚሰሩ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን ተቋማዊ አደረጃጀትን በማጠናከር የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማስተሳሰርና የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የገለጹት። የውሃና መብራት መሰረተ ልማት ችግሮችም በዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ሲሆኑ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጭ ባሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሩ የጎላ እንደነበር ተመልክቷል። ኢንቨስትመንትን ለማጠናክር ማህበረሰቡ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት እንዲይዛቸው ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥና የኢንቨስትመንት ግቦችን ሊያሳካ የሚችል ጥራት፣ ብቃትና ልምድ ያለው ኢንቨስትመንት ማበረታታት እንደሚያስፈልግም ነው የተመለከተው። የወቅቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጋር አብሮ ለመራመድም የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑ ተመልክቷል። ከነዚህም መካከል በመጭው መስከረም ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው የኢንቨስትመንት አዋጁ በጋራ ምክክር መድረኩ የማሻሻያዎች ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ተሳታፊዎችም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማሻሻል በአዋጁ መሻሻልና መካተት አለባቸው የሚሏቸውን ያነሱ ሲሆን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር፣ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች በአዋጁ በትኩረት መታየት እንዳለባቸውም ለአብነት አንስተዋል። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን 40 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የምትሸፍን ሲሆን በአፍሪካ ደረጃም ከግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮንጎና ሞሮኮ ቀጥላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም