የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ የ2012 ማስተግበሪያ ረቂቅ እቅድ ተዘጋጀ

332

ሰኔ 10 / 2011 የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን በትምህርት ዘመኑ ተግባራዊ ለማድረግ የ2012 ማስተግበሪያ ረቂቅ እቅድ መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በአገሪቱ የሚሰጠው ትምህርት እውቀት ብቻ ሳይሆን ተግባርን ያማከለ እንዲሁም አገር በቀል እውቀትና የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ክህሎት ያካተተ እንዲሆን ለማስቻል ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

ሚኒስቴሩ በፍኖተ ካርታው ግኝትና ምክረ ሃሳብ ዙሪያ ከዘርፉ የልማት አጋሮችና በአገሪቱ ከሚገኙ ኤምባሲዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተወያይቷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በውይይቱ ላይ እንዳሉት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በርካታ ውይይቶች ሲካሄድበት ቆይቶ ረቂቁ ተዘጋጅቷል።

ከውይይቶቹ በኃላ ከፍኖተ ካርታው በተጨማሪ ረቂቅ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

የፍኖተ ካርታው የመጀመሪያ ረቂቅና የ2012 ማስተግበሪያ ረቂቅ እቅድ መዘጋጀቱን በቅርቡም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ቀርቦ በቀጣዩ ዓመት ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፍኖተ ካርታው ተጠናቆ በ2012 በአጠቃላይ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ወደ ትግበራ ለመግባት መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

በእዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ በቅርቡ ለኀብረተሰቡ ማብራሪያ እንደሚሰጥም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የልማት አጋሮች በፍኖተ ካርታው ዙሪያ እንዲወያዩ የተደረገው ትግበራው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።

ውይይቱ ስለፍኖተ ካርታው ግንዛቤ ለመፍጠር ከማገዙ ባሻገር በልማት አጋሮች የሚነደፉና የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በፍኖተ ካርታው የተቃኙ እንዲሆኑ የሚያስችል  የልማት ትብብር ለመፍጠር እንደሚረዳም አንስተዋል።

የትምህርት ዘርፉን ሲደግፉ የቆዩ የልማት አጋሮች በበኩላቸው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኬ ማቱሳንጋ መንግስታቸው በተለይ የሂሳብና የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ የተወከለ ሰው በአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ጃፓን የምታደርገውን  ድጋፍ ‘አጠናክራ ትቀጥላለች’ ብለዋል።

በፊንላንድ ኤምባሲ የትምህርት አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሳይ ቫሬን በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው የዘርፉን አቅጣጫ የሚያሳይና በሚገባ የተሰራ ነው ብለዋል።

የልማት አጋሮች የትምህርት ዘርፉ እንዲሻሻል ድጋፍ እያደረግን ነው ያሉት ዶክተር ሳይ በቀጣይ የሚከወኑ ፕሮጀክቶች ሚኒስቴሩ በሚፈልገውና በፍኖተ ካርታው ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው የትምህርት መግቢያ ዕድሜን፣ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ፣ የጥራት ማረጋገጫ ስራዎችና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያካትት ነው።