የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በመቐለ ያስገነባው ኮሌጅ ተመረቀ

65
ሰኔ 10 / 2011የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ያስገነባውን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዛሬ አስመረቀ። ኮሌጁን የመረቁት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልና በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሁንሚን ሊም ናቸው ። የትግራይ ክልል የቴክኒክ ትምህርት ሙያና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ ሀዲሽ እንደገለጹት ኮሌጁ 250 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ድረስ አሰልጥኖ የማስመረቅ አቅም አለው ። ኮሌጁ በብየዳ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በጀኔራል መካኒክ፣ በኮንስትራክሽንና በማሽን ዘርፍ ብቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ሙያተኞችን የማፍራት ተልእኮ ያለው መሆኑንም ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል። ተቋሙ ከኮሪያ የሚመጡ ፈቃደኛ አስተማሪዎችን በመጠቀም ለሌሎች የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጭምር አርአያ ሆኖ እንዲሰራ ይደረጋል ተብሏል ። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በኮሌጁ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር "ከኮሪያ የእድገት መንገዳቸውን በመከተልና ትምህርት በመውሰድ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት እንፈልጋለን" ብለዋል። በኮሌጁ ግንባታ የታየውን ትብብር ወደ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ስራዎች አንዲስፋፋ ፍላጎት መኖሩንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ሁንሚን ሊም በበኩላቸው ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በትምህርትና በመጠጥ ውሃ መስኮች እያደረጉት ያለው ትብብር ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  ተናግረዋል። "ደቡብ ኮሪያ ከኋላቀርነትና ከድህነት ወደ ብልፅግና የተሸጋገረችበት ዋና ምክንያት ለትምህርት ጥራት በከፍተኛ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ በመቻሏ ነው" ሲሉም ጠቁመዋል ። "የኮሪያ የካበተ ልምድ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም