በሰሜን ሸዋ ዞን ከ330 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ

47
ደብረ ብርሃን ሰኔ 10 / 2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ330 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ መምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት ተከላው የሚከናወነው በበጋ ወራት የተቀናጀ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በተከናወነባቸው ተፋሰሶች ነው። በክረምት ወራት  የሚካሄደው ተከላ 35 ሺህ 200 ሄክታር መሬት እንደሚሸፍንም አስረድተዋል፡፡ ችግኞቹን ኅብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ችግኞቹን ተንከባክቦ ለውጤት በማጽደቅም አሁን ያለውን የዞኑን 15 ከመቶ የደን ሽፋን ወደ 16 ነጥብ 2 ከመቶ እንደሚያደርሰው ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ከአምስት ዓመታት በፊት ከለሙት ከአንድ ሺህ በላይ ተፋሰሶች መካከል 520 ተፋሰሶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መሸጋገራቸውን የቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡ የተፋሰሶቹን ዘላቂነት ለማረጋገጥ አርሶ አደሮቹ ተደራጅተው የሚሰሩበት ፈቃድ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሮች በተፋሰሶቹ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የደንና የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉት 189 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 76 ነጥብ 9 ከመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን አቶ ጌታነህ ገልጸዋል፡፡ የአንፆኪያ ገምዛ ወረዳው አርሶ አደር ጌታቸው ቦጋለ በበኩላቸው የዓመቱን ችግኝ ተከላ በጋራና በግል መሬታቸው ለመትከል ተዘጋጅቼያለሁ ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም