ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ

71
ካምፓላ ሰኔ 1/2010 ኢትዮጵያና ኡጋንዳ የኢኮኖሚ ትስስርን ጨምሮ በተለያዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ። የሁለት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ኡጋንዳ ካምፓላ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያይተዋል። በአገሪቱ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ታላቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል። አገሮቹ የሚጋሩት ታሪክ፣ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላቸው ራዕይ፣ የተባበረችና የለማች አፍሪካን የማየት ጽኑ ፍላጎታቸው እንደሚያስተሳስራቸው ነው የተናገሩት። የሁለቱ መሪዎችን ውይይት የተከታተሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት መሪዎቹ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ወስነዋል። መሰረተ ልማትን በማስፋፋትና በኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር አስፈላጊነት ላይ የመከሩት መሪዎቹ በየብስ ትራንስፖርት አገሮችን የማገናኘት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሁለቱ አገሮች ባወጡት ባለ 14 ነጥብ መግለጫ እንደተመለከተው በትምህርት፣ በግብርና፣ በውሃና አካባቢ፣ በሃይል አቅርቦት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርትና ኮሙኒኬሽን፣ በመከላከያ፣ በባህልና ስፖርት ያለቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ተስማምተዋል። መሪዎቹ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ከፍ በማድረጉ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። ለዚህም የግል ዘርፉን ለመሳብ ያሉትን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች መለየት አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል።የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠና የመመስረት ስምምነትና የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በነጻነት የመዘዋወር ፕሮቶኮል መፈረሙ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ እንደሚቆጠር ነው የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ በሚካሄደው 29ኛው የኡጋንዳ ብሄራዊ ጀግኖች በዓል ላይ ከታደሙ በኋላ ወደ ግብጽ ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም