በምዕራብ ጎንደር ዞን ተፈናቅለው የነበሩ አርሶ አደሮች በቀያቸው የመኸር እርሻ ሥራ ጀመሩ

59
ጎንደር ሰኔ 10 / 2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ተፈናቅለው የነበሩ አርሶ አደሮች በቀያቸው የመኸር እርሻ ሥራ መጀመራቸውን ገለጹ፡፡ በዞኑ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ  በመደረግ ላይ ነው፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ እርሻ ሥራቸው የተመለሱት በቀድሞ መኖሪያቸው አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። በቋራ ወረዳ የደላ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አስማረ መንግስቱ በአካባቢያቸው በነበረው አለመረጋጋት ወደ  ማዕከላዊ ጎንደር ላይ አርማጭሆ ወረዳ ከነቤተሰባቸው ተፈናቅለው እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ በአካባቢያቸው ሰላም በመመለሱ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ባለፈው ወር መጨረሻ ተመልሰው የእርሻ ስራቸውን መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነባር ጎረቤቶቻችን በፍቅር ተቀብለው የሚችሉትንም ያህል በቁሳቁስና በገንዘብ እየደገፉን ነው'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል ማለት አይቻልም ያሉት አርሶ አደሩ፣ መንግስት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እሸቱ በላይ በበኩላቸው በግጭቱ ተፈናቅለው ከቆዩበት ሥፍራ በቅርቡ ተመልሰው ሥራቸውን መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ መንግስት ለእርሻ ሥራ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ድጋፍ ቢያደርግላቸውም፣ የዘርና የሌሎች ግብዓቶች እጥረት እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡ በመተማ ወረዳ የቱመት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲሳይ አበጋዝ በበኩላቸው ከተፈናቃይነት ወጥተው በቀድሞው መኖሪያቸው የእርሻ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹መንግስት የመልሶ ማቋቋሙን ሂደት በማፋጠን ሁሉም ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ አለበት›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የመልሶ ማቋቋሙ ግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የዞኑ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚሀም ለተፈናቃዮቹ መገንባት ካለባቸው ከ2 ሺህ 500 ቤቶች ውስጥ 481 ቤቶች ተገንብተው እንዲገቡባቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ያላቸው 2 ሺህ 200 የሚጠጉ አባወራዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በመኸር እርሻ ሥራ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የግብርና ስራ ለጀመሩት የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል። በዞኑ ባጋጠመው የምርጥ ዘር እጥረት ባለመቅረቡ የአካባቢውን ዘር ሕዝቡ ከክምችቱ በማዋጣትና ማህበራት ደግሞ በግዥ እያቀረቡላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዞኑ የተፈናቀሉ 32 ሺህ ሰዎች ሙሉ በመሉ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም