ኅብረተሰቡ ግድቡ ግንባታ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

91
ደሴ ሰኔ 9 ቀን 2011 ኅብረተሰቡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ። የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ከደቡብ ወሎ ዞንና ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች ጋር  ዛሬ በደሴ ከተማ ተወያይቷል። የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ በዚህ ወቅት እንደጠየቁት ኅብረተሰቡ በግድብ ግንባታ ያደረገውን ተሳትፎ አሁንም አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል። ግድቡ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ  ግንባታው እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ያደረገውን ድጋፍና ተሳትፎ ማጎልበት ይገባዋል ብለዋል። የግድቡን  ግንባታ ለማጠናቀቅ ከ130 እስከ 150 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግድቡ ያለበትን ደረጃ በማሳወቅ  መነቃቃት እየተፈጠረ መሆኑን ያወሱት ወይዘሮ ሮማን፣የግድቡ ግንባታ 66 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። ከኅብረተሰቡ በያዝነው ዓመት 800 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል። እስካሁን ከሕዝብ የተሰበሰበው መዋጮ 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መድረሱን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ብቻ 81 ቢሊዮን  ብር የሚገመት የጉልበት ሥራ በነጻ ማከናወኑን ገልጸዋል። እንደ ወይዘሮ ሮማን ገለፃ ግድቡ አገራዊ አንድነትን ፣ሰላምንና ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሯል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ለግንባታው  እስካሁን ከ99 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል። በፕሮጀክቱ አዳዲስ የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ገብተው መሥራት መጀመራቸውን ተናግረዋል። ''ግድቡ እስከ 100 ዓመት የማገልገል አቅም እንዲኖረው የጥራት ችግር የታየባቸውን አሰራሮች እያስተካከልን ነው''ብለዋል። የፌዴራሉ መንግሥት ለግድቡ ግንባታ አፈጻጸም የሥራ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ የሱፍ የዞኑ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል ጥረቱ እንደሚጠናክር አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም