በሰቆጣ በግለሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

163
ሰኔ 9/2011 በሰቆጣ ከተማ ዛሬ በግለሰቦች መካከል የተነሳ ግጭት ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ የከተማው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሻምበል ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ በከተማው በ02 ቀበሌ ቀጠና 6 በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት የሶስት ልዩ ኃይል አባላት ህይወት ሲጠፋ በአንድ ግለሰብና በአንድ የማረሚያ ቤት ፖሊስ ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። በአደጋው የቆሰሉ ሰዎች በከተማው ተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ግጭቱን ለማስቆምና ለመገላገል ሲሞክሩ ህይወታቸው ያለፈው የልዩ ኃይል አባላት አስከሬንም በክብር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደተላከ ተናግረዋል። በግጭቱ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም ተናግረዋል። የተፈጠረው ችግር በግለሰቦች መካከል እንደመሆኑ መጠን ከተማውን ወደነበረበት ለመመለስ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ የጸጥታ አካላትና የልዩ ኃይል ሰዎች  የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም