ኮሚሽኑ ዘንድሮ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን ገለጸ

131
አክሱም ሰኔ 9/2011 በኢትዮጵያ ባለፉት 11 ወራት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ። ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ሙሉጌታ በየነ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአክሱም ከተማ እየተካሄደ  ባለው ውይይት ላይ እንደተናገሩት ንብረቱ  የተያዘው ከውጭ ሲገባና ከአገር ሲወጣ ነው ። ለዚህም ዋነኞቹ  ምክንያቶች የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ደካማነት ፣ በተዋናዮቹ ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ አለመውሰድና ለህጋዊ ንግድ ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ ነው ብለዋል። ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ  ጉዳት የሚያስትለው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተው፣ችግሩን ለመከላከል የአሰራርና የኬላ አደረጃጀቶች በመፈጠር ላይ መሆናቸውን  አስረድተዋል። ኮሚሽኑ በአጥፊዎች  ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለሕዝብ ማሳወቅ መጀመሩንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ብቻ 899 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በማሳያነትም አቅርበዋል። የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አበበች አቤቤ በበኩላቸው መድረኩ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ለመስራትና የጋራ መፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። የአገሪቱ የግብርና ምርቶች፣ ማዕድንና የቁም እንስሳት በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ስለሚወጡ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴውን እየጎዱት መሆኑን አመልክተዋል። በአገሪቱ ከ2006-2010 ባለው ጊዜ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሕገ ወጥ ዕቃዎች መያዛቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም