የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው ነው - ምሁራን

46
አክሱም ሰኔ 1/2010 በአትዮ - ኤርትራ  መካከል ተፈጥሮ  ለቆየው የሰላም ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው መሆኑን ምሁራን ገለፁ፡፡ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው ነው ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፖቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አጽብሃ ተክለ እንዳሉት ስራ አስፈጻሚው ''የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እቀበለዋለሁ'' ማለቱ መንግስት ለሰላም ያለው ዝግጁነት ያሳያል ፡፡ በቀጣይም በአፈጻጸሙና አተገባበሩ ዙሪያ ከህዝብ ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ''የኢህአደግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰደውን አቋም የኤርትራ መንግስት በመቀበል የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ሰላም ማረጋገጥ ይገባል'' ብለዋል፡፡ ''ከሁሉም በፊት ሰላም ሊሰፍን የሚችለው  በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱንም ህዝቦች በማወያየት እንጂ ድንበር በማካለል አይደለም'' ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሁለቱም ወድማማች ህዝቦች የጠነከረ ወዳጅነት ወደ ነበረበት ለመመለስ  ህዝቡ ማወያየት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የኢህደግ ስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉ ለሰላም ያለውን ዝግጁነት ያሳያል ያሉት ደግሞ  በዩኒቨርስቲው  የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሓዱሽ ረዳኢ ናቸው። ውሳኔው የሁለቱም አገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ''ችግሩ በድንበር ብቻ የተፈጠረ ባለመሆኑ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሁለቱም መንግስታት መካከል ያሉ ችግሮችን በጥልቀት መርምሮ ለመፍታት ቁርጠኝነት ይጠይቃል'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም