ካሳለፍነው የታሪክ ጠባሳ በመማር ነገን የተሻለ ለማድረግ መስራት ይገባናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

168
ሰኔ 8/2011 ዜጎች በእምነታቸውና በአስተሳሰባቸው ሲሳደዱበት ከነበረው አስከፊ ታሪካችን ተምረን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በደሴ ከተማ ተገኝተው ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ  ክልል ርዕሰ  መስተዳደር  ዶክተር አምባቸው መኮንን እና  ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። ነዋሪዎቹ በውይይቱ አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ያነሱ ሲሆን፤ ስራ አጥነት፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ የመሰረተ ልማት  አለመሟላት በመድረኩ በስፋት የተንሸራሸሩ ጥያቄዎች ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በምላሻቸው በአዲሱ በጀት ዓመት የአካባቢውን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ከዚህም ውስጥ በደሴ የሚገነባው ሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል አንዱ መሆኑን አውስተዋል። ነገር ግን ሆስፒታሉ በተደጋጋሚ የሚነሳው የወሎ ተሪሸሪ ሆስፒታል አለመሆኑን በግልጽ አስረድተዋል። ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ ለክልሎች ሰፊ በጀት እንደሚመደብ ገልጸው፤ ክልሎች ይህን ሃብት በሚፈለገው አግባብ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ዜጎች በእምነታቸውና በአስተሳሳባቸው ምክንያት የሚሰደዱበት ጥቁር ታሪክ እንዳሳለፈች ያስታወሱት  ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''ሁላችንም ከዚህ አስከፊ ታሪክ በመማር የተሻለ ነገን መገንባት ይገባናል'' ብለዋል። የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ መንግስት ብቻውን የሚከውነው እንዳለሆነ ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን  እንዲወጣ አሳስበዋል። በማፈናቀል፣ ግድያ፣ ዘረፋና በሌሎች ህገወጥ ተግባር ተሰማርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል። በቀጣይ መንግስት ህግ የማስከበሩን ተግባር አጠናክሮ እንደሚሰራ ቃል በመግባት። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የወሎ ነዋሪዎች የቀደመ የአብሮነትና መቻቻል እሴታቸውን  ለአፍታ እንኳን ሳይለቁ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ከውይይቱ  በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በውይይቱ የተካፈሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች  በተካሄደበት  አይጠየፍ አዳራሽ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል። በውይይቱ የተገኙ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች የወሎ የባህል አልባሳትና  የበግ ስጦታ ከአካባቢው አስተዳደርና ማህበረሰብ ተበርክቶላቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም