አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በሞሮኮ ራባት ከተማ በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷል

204
ሰኔ 8/2011  አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ነገ በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው የ 1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷል። የ2019 ስድስተኛው ዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ በራባት ከተማ 52 ሺህ ተመልካች በሚያስናግደው የልዑል ሙላይ አብደላህ ስታዲየም ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ ይካሄዳል። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የአሸናፊነቱን የቅድሚያ ግምት አግኝታለች። አትሌት ገንዘቤ በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው አራተኛው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር 3 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ከ28 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የ2019 የርቀቱን ፈጣን ሰአት በማስመዝገብ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። አትሌት ገንዘቤ እ.አ.አ በ2015 በፈረንሳይ ሞናኮ በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ በተካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር 3 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆኗም አይዘነጋም። በነገውም ውድድር አትሌት ገንዘቤ ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ እንዳገኘች የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድ ገጹ አስፍሯል። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣ አትሌት አክሱማዊት አምባዬ እና አትሌት ለምለም ሃይሉ ከአትሌት ገንዘቤ በተጨማሪ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣ ኬንያውያኑ አትሌቶች ዊኒ ቺቤት እና ጆስፊን ኪፕላንጋት እንዲሁም ሞሮኮዋዊቷ አትሌት ራባቤ አራፊ የአትሌት ገንዘቤ ዋንኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን በሪሁ፣ አትሌት መለሰ ብርሃንና አትሌት አቤ ጋሻሁን የሚሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የውድድሩን የአሸናፊነት ግምት ወስደዋል። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች አትሌት ጌትነት ዋለ እና አትሌት ጫላ በዮ የሚሳተፉ ሲሆን በውድድሩ የኬንያና ሞሮኮ አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል። በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ታደሰ ለሚ የሚካፈል ሲሆን ኬንያዊው አትሌት ቪንሰንት ኪቤት የአሸናፊነቱ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቶታል። በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ሀብታም አለሙ የምትሳተፍ ሲሆን ኬንያውያኑ አትሌቶች ኔሊ ጄፕኮስጌይ እና ኤሚሊ ቼሮቲች እንዲሁም የታላቋ ብሪታኒያ አትሌት ሊንዚ ሻርፕ እና ሞሮኮዋዊቷ አትሌት ማሊካ አካኡዊ ውድድሩን የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሚሳተፉባቸው ውድድሮች በተጨማሪ ነገ በራባት ከተማ ሌሎች የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ይካሄዳሉ። የ2019 ሰባተኛው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በአሜሪካ ኢውጂን ከተማ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ 14 ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራሰልስ በሚካሄደው ውድድር ይጠናቀቃል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሬሽኖች ማህበር በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአጠቃላይ የስምንት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ በ16 የተለያዩ የውድድር አይነቶች በእያንዳንዱ ርቀት የአጠቃላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የ50 ሺህ ዶላር እና የዳይመንድ ሽልማት ያገኛል። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ርቀት አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከመስከረም 17 እስከ  መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለማጣሪያ የሚሳተፉ ይሆናል። ከዚህም ባለፈ በእያንዳንዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ የ100 ሺህ ዶላር ሽልማትም ተዘጋጅቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም