ሕብረተሰቡ በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለሚፈጥሩ ኃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን አይገባም…አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ

144

ሰኔ 8/2011   በብሔርና በሃይማኖት ስም ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ በሚኖር ህዝብ መካከል ቅራኔ በመፍጠር ፍላጎታቸውን ለማሳካት ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ህብረተሰቡ መጠቀሚያ  እንዳይሆን ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ተገለጸ።

በሀላባ ዞን በእስልምናና በፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች መካከል አንድነትን ማጠናከር የሚያስችል የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ የዕርቅና የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እንዳሉት ሰላምን ማስጠበቅ ለሌላ ሰው የሚሰጥ ተግባር አይደለም።

“መላው ህብረተሰብ ከአዕምሮው የሚመነጭው በመሆኑ ከውስጣችን ሰላምን መፈለግና ለሰላም መስራት ይገባል” ብለዋል።

በተለይ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ምክንያቶችንና አመለካከቶችን በመለየት መታገል እንደሚገባ ነው አቶ ሚሊዮን የጠቆሙት።

“የክልሉ ህዝቦች የተለያየ ዕምነት ፣ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያለን በመሆኑ ይህን በአግባቡ በመያዝ ለዘመናት ተቻችሎ የመኖር ልምዳችንን ልናጎለብት ይገባል” ብለዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ እርስ በእርስ በመረዳዳት ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረገ ጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ሳያጣሩ በመቀበል በሀላባ ቁሊቶከተማና ዙሪያዋ በቤተ ዕምነት ላይ የተፈጸመው ተግባር ተገቢ እንዳልሆነም አቶ ሚሊዮን  ተናግረዋል።

የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑ ህዝቦች በጋራና በፍቅር በሚኖሩባት የሀላባ ዞን ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ችግር ተከስቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

የቁሊቶ ከተማ ነዋሪዎች በጋራ ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩባትና ሀብት ያፈሩባት ከተማ መሆኗን ጠቁመው ነዋሪዎቿ በዕምነት ሳይከፋፈሉ  እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍም ሆነ ሰርቶ መኖር አይቻልም” ያሉት ወይዘሮ ሂክማ በህብረተሰቡ መካከል የቀድሞ አንድነትና አብሮነት ተመልሶ እንዲመጣ ወላጆች ልጆቻቸውን መምከር፣ ማስተማርና በመልካም ስነምግባር ማነጽ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የቁሊቶ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አልዬ በበኩላቸው “ባለፈው የካቲት 2 ቀን 2011ዓ.ም በዱራሜ ከተማ አንድ መስጊድ ተቃጠለ የሚል የሀሰት ወሬ መወራቱን ተከትሎ በከተማዋ የተፈጠረው ችግር የከተማዋን ነዋሪዎች ያሳዘነና አንገት ያስደፋ ነበር” ብለዋል።

በወቅቱ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ንብረት ላይ በቃጠሎ ውድመት መድረሱን ጠቁመው፣ የከተማ አስተዳደሩ ከዞኑ አስተዳደርና ከጸጥታ አካላት ጋር ባደረገው ርብርብ የከፋ ጉዳት ሰይደርስ ችግሩን  መከላከል እንደተቻለ አስታውሰው

የጸጥታ ኃይሉ ከችግሩ ጋር ተያይዞ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል እያጣራ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅት 10 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አራቱን የከተማው ነዋሪዎች ባዋጡት ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተጠግነው ወደ አምልኮ ሥራቸው መግባታቸውን ጠቁመዋል።

ቀሪዎቹን ለመጠገን ህዝቡ ቁሳቁስና ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሀላባ ቁሊቶ በተካሄደው የዕርቅ የሰላምና የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስ ላይ ከዞኑ፣ ከደቡብ ክልልና ከፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች የዕስልምናና የክርስትና ዕምነት መሪዎችና ተከታዮቻቸው ተሳታፊ ሆነዋል።