ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከደሴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

129
አዲስ አበባ   ሰኔ 8 /2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ከደሴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይት መድረኩ የተሳተፉት የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ስራ አጥነት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የህግ የበላይነት አለመከበርን በተመለከተ ጥያቄዎች አንስተዋል። ነዋሪዎቹ የመንገድ፣ ኤሌክትሪክና ሆስፒታል አገልግሎት በተሟላ መልኩ እንዲቀርብላቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። ከነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ''የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ለመጀመር በጀት ተይዟል'' ብለዋል። መንግስት የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ስርጭት ለማሻሻል የሚያስችል ጥረት መጀመሩን ገልጸው በዚህም የደሴ ከተማም ተጠቃሚ እንደምትሆን ተናግረዋል። የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄውን ለመመለስ በመጪው በጀት ዓመት ከተያዙ አጠቃላይ ፕሮጀክቶች መካከል ከሐይቅ እስከ ጭፍራ የሚዘልቀው መንገድ አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል። በመጨረሻም የወሎ ህዝብ የሚታወቅበትን የመቻቻል እሴት ጠብቆ መቆየት እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መክረዋል። በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም