በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉን መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን አጠበበ

64
ሰኔ 8/2011  በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉን መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን አጥብቧል፡፡ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተካሄደዋል። ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከል የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተከታዩ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ነው። የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን 28 ለ 25 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተዳክሞ በታየበት በዚህ ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው ክለብ የተሻለ ነበር። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከፍተኛ የሃይል ፍትጊያና ሽኩቻ የነበረበትና በተጫዋቾች በሚሰሩ ጥፋቶች ጨዋታው በአጭር የጊዜ ልዩነት ሲቋረጡ ተስተውሏል። በጨዋታው ላይ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተወሰኑ ተጫዋቾች የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ሲያሳዩ የነበረው ተግባርም ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ድርጊት ነው። የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች የዳኛ ውሳኔ ላይ ስህተት አለ በማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ጨዋታው ኮሚሽነር በመሄድ ቅሬታ ሲያቀርቡም ታይቷል። በጨዋታው ሁለተኛ ክፍለ ጊዜ ተጭኖ የተጫወተው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ተጋጣሚው የግብ ቀጠና በመድረስና የግብ እድሎችን በመፍጠር በሰፊ የግብ ልዩነት መምራትም ችለው ነበር። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ልዩነቱን ቢያጠብም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውጤቱን በማስጠበቅ አሸናፊ መሆን ችሏል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በስታዲየሙ የተሻለ የተመልካች ቁጥር የተከታተለው ሲሆን የክለቦቹ ደጋፊዎችም ቡድናቸውን በጥሩ ሁኔታ ሲያበረታቱም ለማየት ተችሏል። ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 28 ከፍ በማድረግ ከመሪው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ አድርጓል። እስከዛሬው ጨዋታ ድረስ ያደረጋቸውን ሁሉንም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በማሸነፍ በስኬት ጉዞ ላይ የነበረው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል። የሶስት ሳምንት መርሃ ግብር በቀረው የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት የሚደረገው ፉክክር ተጠባቂና አጓጊ አድርጎታል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ መከላከያ ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 40 ለ 24 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የፕሪሚየር ሊጉ 18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ሲቀጥል መቐለ ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከከምባታ ዱራሜ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ18ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ፌደራል ፖሊስ ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ቡታጅራ ከተማ በጨዋታ ሜዳዎች ላይ ባለመገኘት በተደጋጋሚ ጊዜ የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ  ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጪ እንዲሆንና በቀጣይ ከክለቡ ጋር ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በፎርፌ ውጤት እንዲያገኙ ባለፈው ሳምንት መወሰኑ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት ፌደራል ፖሊስ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። ድሬዳዋ ከተማም በፋይናንስ ችግር ምክንያት ራሱን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በውድድሩ ደንብ መሰረት ከድሬዳዋ ጋር ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች የፎርፌ ውጤት እያገኙ ነው። ጎንደር ከተማ በ18ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ የማያደርግ በመሆኑ አራፊ ክለብ ነው። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በሊጉ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ28፣  መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ22 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም