በ13 ነጥበ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ዘጠኝ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

139
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በአገሪቱ የመንገድ ሽፋን ተደራሽነትን ለማሳደግ በ13 ነጥበ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ በአጠቃላይ 749 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ዘጠኝ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ለማካሄድ ስምምነት ተፈረመ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጨረታው ወጥቶ አሸናፊ መሆን የቻሉ የአገር ውስጥና የውጭ መንገድ ስራ ተቋራጮች ግንባታውን ለማካሄድ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። የግንባታ ወጪ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት በጀት እንደሚሸፈን ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው። ሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከጀመረበት 2008  እስከ ሚያዚያ 30 2010  ባለው የሁለት ዓመት ከአስር ወራት ጊዜ ውስጥ 7ሺህ910 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አዳዲስ የመንገድ ግንባታና ከባድ ጥገና መደረጉን ጠቁመዋል። በስምምነቱ በአማራ ክልል የደባርቅ ዛሬማ (የሊማሊሞ አማራጭ መንገድ)፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሐረር ኮምቦልቻ ቦምባስ ኤጀርርሳ ጎሮ አህመድ ኢማም፣ በሶማሊ ክልል አፍዴራ ዞን የጨረቲ ጎሮ በክሳ ጎርዳምሌ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ከሃገረ መኮር እስከ ኩንዲና በደቡብ  ክልል የሺሺንዳ ቴፒ መንገድ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም በሶማሊ ክልል የሚገኘው የፊቅ ሃሜሮ መንገድ ፕሮጀክት፣ በደቡብ ወሎ የሚገኘው ጉጉፍቱ-ወረኢሉ ደጎሎ መንገድ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነቀምት ሶጌ ካማሽ ቆንሾ መንግድ ግንባታቸው የሚካሄድ ይሆናል። በአማራ ክልል የሚገኘው የዳባት ቀራቀር ከተማ ንጉስ ዲዛይንና ግንባታ መንገድ ፕሮጀክት ክፍል የሆነው አጅሬ ቀራቀር ከተማንጉስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትና በኦሮሚያ ክልል ባቢሌ ዞን የሮቤ ጋሴራ ጊኒር መንገድ ዲዛይንና ግንባታ ፕሮጀክቶች ስምምነት ተፈርሟል። ከመንገዶች ግንባታ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ሲያጋጥሙ የቆዩና ለግንባታ መዘግየት ምክንያት የነበሩ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ስርዓት በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን  የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉን ጥሪ አቅርበዋል። የመንገዶቹ ግንባታ ከ3 እስከ 4 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አርዓያ ግርማይ ጠቅሰዋል። ጨረታውን አሸንፈው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ስምምነቱን የተፈራረሙ ስራ ተቋራጮችም የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። የስራ ተቋራጭ ተወካዮች በበኩላቸው ግንባታዎችን በጥራትና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለማስረከብ በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም