ረቂቅ አዋጁ ህብረተሰቡ የሚተማመንበት የፍትህና የፍርድ ቤት ስርዓት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል

78
ሰኔ 8/2011 በዳኝነት አስተዳዳር ላይ እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ አዋጅ ህብረተሰቡ የሚተማመንበት የፍትህና የፍርድ ቤት ስርዓት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ። ፍርድ ቤቱ በዳኝነት ሥርዓቱ ማሻሻያ አማካሪ ቦርድ እያዘጋጀ ባለው "የዳኝነት አስተዳዳር ረቂቅ አዋጅ"  ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ውሳኔዎች በህጉ መሰረት ሳይሆኑ ለአንድ ወገን ያደሉ ናቸው በሚልና እስካሁን የዳኝነት ስርዓት ውስብስብ ነው በሚል ባልተገቡ አሰራሮች ስሙ ሲነሳ ነበር። በመሆኑም በፍርድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በተለይም ከዚህ ቀደም በነበረው በ684/2002 አዋጅ ያልተዳሰሱ ጉዳዮችን ለማሻሻል አማካሪ ቦርድ ተዋቅሮ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል። ረቂቅ አዋጁ ወደ ስራ ሲገባም በዳኝነት አስተዳዳር ላይ የሚሰተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት ህብረተሰቡ የሚተማመንበት የፍርድ ቤት ስርዓት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል። ረቂቅ አዋጁ ዳኞች በሚሰሩት ስራ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ተአማኒነት እንዲኖራቸው እንዲሁም በበጀትና በሰው ሃይል አሰተዳደር እራሳቸውን ችለው እንዲተዳደሩ ለማስቻል መሆኑንም አክለዋል። ረቂቅ አዋጁ ከዳኝነት ሥራ ውጭ ያሉ የፍርድ ቤት ሰራተኞች ፍርድ ቤቱ እራሱ እንዲመለምልና እንዲያስተዳደር በማድረግ የፍርድ ስርዓቱ ቀልጣፋ፣ፈጣንና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑንም  አብራርተዋል። የረቂቅ ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማንደፍሮ በላይ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ፍርድ ቤቶች ከውጫዊና ውስጣዊ ጫና ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ያደርጋል ብለዋል። ፍርድ ቤቱ በሰውና በበጀት አመዳደብ እራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ፣ የዳኞች ሹመት ግልጽና፣ የዳኝነት ስርዓቱ የህግ የበላይነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ይደነግጋል። በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ረዳት ዳኞች አየተባሉ የሚሰየሙ ቢኖሩም በህግ ያልተደገፈ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው ረቂቅ አዋጁ ረዳት ዳኞች የሚል ደረጃ ሰጥቶ በህግና ስርዓት እንዲሰሩ ለማድረግም ይረዳል። የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት ከዳኞች፣ ከጠበቆች፣ከተዋቂ ሰዎችና ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚወከሉ ሆነው ቁጥራቸው 16 ይሆናልም ብለዋል። ዳኞች ከፖለቲካ ገለልተኛ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ አቋም እንዳያራምዱ፣ ከፖለቲካና ከአክቲቪዝም እንዲቆጠቡና በጡረታ ወይም ከዳኝነት እስከሚወጡ ድረስ ተደራቢ ስራ እንዳይሰሩ በረቂቅ አዋጁ መከልከሉን አስረድተዋል። ረቂቅ አዋጁ የህዝብ አስተያየት ግብዓት ከተካተተበት በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ እንደሚፀድቅም ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም