መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው….የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት

215

ሰኔ 8/2011 በኦሮሚያ ክልል መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በባሌ ዞን መዳወላቡ ወረዳ ከ 61 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የመዳወላቡ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በይፋ ተመርቋል።

አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት የክልሉ መንግስት መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

“ምረቃው የኦሮሞ ህዝብ በ16ኛው ክፈለ ዘመን የገዳ ስርአቱን ባደሰበት የመዳወላቡ ታሪካዊ ስፍራ መሆኑም ልዩ ያደርገዋል” ብለዋል።

አቶ ሽመልስ የባሌ ህዝብ ለፀረ ጭቆና አገዛዝ ያልተንበረከከና የኦሮሞ ህዝብ የትግል ቁንጮ መሆኑንም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

አዲሱ ትውልድም የጀግኖች አባቶቹን አርአያ በመከተል በሀገሪቱ የተጀመሩ ለውጦች ከግብ እንዲደርሱ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለሆስፒታሉ ግንባታና የሕክምና መሳሪያዎች ማሟያ ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል ።

የግንባታ ሥራው በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ በ2009 የተጠናቀቀው ይህ ሆስፒታል ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ለህብረተሰቡ በተወሰነ ደረጃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱም ተመልክቷል።

ሆስፒታሉ ለተለያዩ የሕክምና አገልግሎት መሰጪያ የሚውሉ ከ35 የሚበልጡ ክፍሎች እንዳሉት ተገልጿል።

ዶክተር ደረጄ እንዳሉት ለሆስፒታሉ 12 የመጀመሪያ ደረጃ ዶክተሮችን ጨምሮ ከ160 የሚበልጡ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ተመድበዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሆስፒታል በመደወላቡ ወረዳ የሚገኙትን ነዋሪዎች ጨምሮ በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ለሚገኙ በጠቅላላው ከ160 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል።

ሆስፒታሉ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚያካትተውን የቀዶ ሕክምና መስጪያ፣ እንዲሁም ለተኝቶና ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎች አሉት ።

በተጨማሪም ዘመናዊ የራጅ፣ አልትራሳውንድና ተያያዥ መሳሪያዎች እንዲሟሉለት መደረጉን ለማውቅ ተችሏል ።

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ የዞን አመራሮችና የወረዳው የህዝብ ተወካዮች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የኢትዮያ ዜና አገልግሎት ነው።