ኒውዚላንድ ኢትዮጵያ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት ትደግፋለች

78
ሰኔ 8/2011 ኢትዮጵያ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት ኒውዚላንድ እንደምትደግፍ አስታወቀች። ኒውዚላንድ በኢትዮጵያ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ማርክ ራምስደን ገለጹ። አምባሳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለይም በፖለቲካው መስክ የታየውን ለውጥ አድንቀዋል። አምባሳደር ማርክ ራምስደን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኒውዝላንድና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታይ የዘለቀ የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሏቸው። ኢትዮጵያ የጣሊያንን ወረራ በመቃወም በ"ሊግ ኦፍ ኔሽን" አቤቱታ ስታቀርብ ኒውዚላንድ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ያላትን ጽኑ አጋርነት አሳይታለች። ይህም የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ከየት እንደጀመረ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ''በዘመናዊው ዓለምም ኢትዮጵያና ኒውዚላንድ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች ናቸው'' ብለዋል። ኒውዚላንድ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከከፈተችበት ከሰባት ዓመት ወዲህ ባሉት ጊዜያት የሁለትዮሽ የምጣኔ ሃብት ትብብራቸው እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተዋል። ለአብነትም ሥመ-ጥር የኒውዚላንድ የግብርና ውጤት አቅራቢዎች ፎንቴራ እና ኤል አይ ሲ የተሰኙት ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት መሰመራታቸውን ጠቁመዋል። አሁን ደግሞ ኒውዚላንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎትን ተከትሎ በእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል መስክ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኒውዚላንድ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በተናጠል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ኒውዚላንድ በዋነኝነት ከምትታወቅበት የግብርና ውጤቶች ልማት በተጓዳኝም በቴክኖሎጂው  ዘርፍ አንድ የኒውዝላንድ የሬዲዮ ኩባንያ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን መንግሥት ካረጋገጠ በርካታ የኒውዚላንድ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ እምነታቸውን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላበፖለቲካው መስክ ያሳየችው ለውጥ አገራቸው በአድናቆት የሚመለከተው መሆኑን ተናግረዋል። ያም ሆኖ አሁንም በርካታ ችግሮች ከፊት እንደሚያጋጥሙ በመረዳት ለውጡን ከታለመለት ግብ ለማድረስ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ኒውዚላንድ በአፍሪካ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ መሆኗን ገልጸው የገንዘብናየሙያ ድጋፍ በመስጠት የአፍሪካ ኅብረትን ታግዛለች ብለዋል። ኒውዚላንድ በደቡብ ፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኝ ደሴት ላይ የተመሰረተች አገር ስትሆን አምስት ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ አላት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም